ኢትዮጵያ ሜዳልያ የምትጠብቅበት የሴቶች 10 ሺ ሜትር

You are currently viewing ኢትዮጵያ ሜዳልያ የምትጠብቅበት የሴቶች 10 ሺ ሜትር

AMN-መስከረም 03/2018 ዓ.ም

የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመም (ትራክ) ውድድሮች ዛሬ ሲጀምሩ የሴቶች 10 ሺ ሜትር ፍፃሜ በጉጉት ይጠበቃል።

ሦስቱን ሜዳልያ ለመውሰድ የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ይፋጠጣሉ።

ኢትዮጵያ በቡዳፔስት አሸናፊ የነበረችው ጉዳፍ ፀጋይ ጨምሮ በአራት አትሌቶች ትወከላለች።

ፅጌ ገብረሰላማ ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ፎትየን ተስፋዬ የበለጠ ልምድ ካላት ጉዳፍ ፀጋይ ጋር በመሆን ለሀገራቸው ሜዳልያ የማምጣት ሀላፊነት ወስደዋል።

በርቀቱ ኢትዮጵያ ይበልጥ ጉዳፍ ላይ ጥገኛ ትሆናለች። የ28 ዓመት አትሌቷ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለት ወርቅ ፣ አንድ ብር እና አንድ ነሃስ ማግኘት ችላለች።

ከጉዳፍ በመቀጠል የተሻለ ልምድ ያላት እጅጋየሁ ታዬ ከሁለት ዓመት በፊት በቡዳፔስት ያመጣችው የነሀስ ሜዳልያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያገኘችው ብቸኛ ሜዳልያ ነው።

ፎትየን ተስፋዬ እና ፅጌ ገብረሰላማ ሜዳልያ የሚያስገኝ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ያልቻሉ አትሌቶች ናቸው።

የኢትዮጵያውያን ተፎካካሪ ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው ቤትሪስ ቼቤት ናት።

የ10 ሺ እና 5 ሺ ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ኬንያዊቷ አትሌት ከዓመት በፊት በተደረገው የፓሪስ ኦሊምፒክ ሁለት ወርቅ ማምጣቷ ይታወሳል።

ተጠባቂው ፉክክር ቀን 9:30 ይጀምራል።

ዛሬ በሚከናወኑ ሌሎች ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።

ቀን 6:05 በሚጀምረው የ3 ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ በለሜቻ ግርማ ፣ ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬው ትወከላለች።

ድርቤ ወልተጂ በታገደችበት በሴቶች 1500 ሜትር ማጣሪያ ሳሮን በርኸ እና ፍሬወይኒ ሀይሉ ይሳተፋሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review