በሁለት ዓመቱ አንዴ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ ከሚገቡ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡
በውድድሩ የገዘፈ ስም ያላት ኢትዮጵያ ዘንድሮ በጃፓን ቶክዮ በሚደረገው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም ትጠበቃለች፡፡
እኤአ 1983 ላይ በፊላንድ ሄልሲንኪ በጀመረው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ 18 ጊዜ ተሳትፋለች፡፡ የዘንድሮው ለ19ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡
በመድረኩ በርካታ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በ18ቱ ተሳትፎዋ 35 ወርቅ ፣ 38 ብር እና 31 ነሃስ በአጠቃላይ 104 ሜዳልያዎችን በብርቱ አትሌቶቿ ታግዛ አሳክታለች፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ውድድር በ2022 አሜሪካ ሂውጅን የተደረገው ነው፡፡ 4 ወርቅ ፣ 4 ብር እና 2 ነሃስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአሜሪካ ምድር ያገኟቸው የሜዳልያ ብዛት ናቸው፡፡

በግለሰብ ደረጃ እንደ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ በርካታ ሜዳልያ ያስገኘ አትሌት የለም፡፡ ጥሩነሽ 5 ወርቅ እና 1 ብር ስታስገኝ ፤ ቀነኒሳ በቀለ 5 ወርቅ እና 1 ነሃስ አምጥቷል፡፡ ሃይሌ ገብረስላሴ ፣ መሰረት ደፋር ፣ አልማዝ አያና እና ጉዳፍ ፀጋይ በበርካታ ሜዳልያ ሀገራቸውን ከፍ ያደረጉ አትሌቶች ናቸው፡፡
በውድድር ዘርፍ ደግሞ የኢትዮጵያ ትልቁ ባለውለታ 10 ሺ ሜትር ርቀት ነው፡፡ በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ 43 ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ በሴቶች 23 ፣ በወንዶች 20 ሜዳልያዎች ማግኘት ተችሏል፡፡ 5 ሺ ሜትር እና ማራቶን ሌሎች ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ የውድድር አይነቶች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በቶኪዮ ውድድርም በተለመዱ ርቀቶች ትጠበቃለች፡፡
ሻምፒዮናው ነገ በይፋ ሲጀምር ኢትዮጵያ በወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ፣ በሴቶች 1500 ሜትር ማጣሪያ እና በሴቶች 10 ሺ ሜትር ፍፃሜ ላይ ትካፈላለች፡፡
በአጠቃላይ ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው ውድድር ላይ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ተካፋይ ትሆናለች፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ