የከተማዋን ፅዳትና ውበት በዘላቂነት በማስጠበቅ ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን መፍጠር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ገለፁ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ቤቶች የትምህርት ማስጀመሪያ የፅዳት ንቅናቄ ዘመቻ በልደታ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል።

ይህ ከተማ አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ንቅናቄ ፅዱና ጤናማ አካባቢን በአዲስ ዓመት ለልጆቻችን እናስረክብ በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደ ነው፡፡
የ2018 ዓ.ም የትምህርት ቤቶች የትምህርት ማስጀመሪያ የፅዳት ንቅናቄ ዘመቻ መርሃግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር፤ በዛሬው እለት የተካሄደው የፅዳት ዘመቻ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚካሄድ እና ምቹ የመማር ማስተማር የመፍጠሩ ሂደት አንዱ አካል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ላይ የምንሰራው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም አለዉ ሲሉ አቶ ሳዲቅ ሽኩር ገልፀዋል፡፡
በኮሪደር ልማት የታዩ ከተማዋን የማስዋብ ስራ እንደሞዴል በመውሰድ ብሎክና መንደሮቻችንንም በቋሚነት ፅዱና ውብ የማድረጉ ተግባር ሁልጊዜም ሊከናወን ይገባል ያሉት ደግሞ የልደታ ክ/ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አራርሳ ድሪባ ናቸው።
በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉ የትምህርት ማህበረሰብ አካላትም ዘመቻው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በሚመጡ ጊዜ በአዲስ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ የሚረዳ እና ፅዱ የመማር ማስተማሪያ ስፍራ እንዲኖር የሚያስችል ነው ብለዋል።
የ2018 ዓ.ም አዲሱ የትምህርት ዘመን መስከረም አምስት ቀን 2018 ዓ.ም በከተማዋ በሚገኙ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚጀመር መሆኑ ይታወቃል።
በታምሩ ደምሴ