የህዳሴ ግድብ በጋራ ስንተም ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የውይይት መድረኩን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጋራ ስንተም ማንኛውንም ነገር ማሳካት እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም የግድቡ መጠናቀቅ ትልቅ ድል ነው፤ ለዚህ ስለበቃን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት 14 ዓመታት ያለፈበትን ውጣ ውረድ፣ የተገኙ ድሎች፣ የውሃ ፖለቲካ ምንነት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሁፎች ቀርበው ወይይት እየተካሄደባቸው ነው።
ከፓናል ውይይቱ ጎን ለጎን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለፈበትን ሁኔታ የሚያሳይ የፎቶ አውደርዕይም ክፍት ተደርጓል።
በሃብታሙ ሙለታ