የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ላይ መዋሉ ለኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ምላሽ፤ ለእኔ ደግሞ እንደ አመራር ትልቅ ኩራት ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
በጋራ ከቆምን፣ ከፀናን፣ ቆርጠን ከሠራን ነገም ወደፊትም የማንችለው ምንም ነገር እንደሌለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ትልቅ ማሣያ ነው ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትደጵያ ማንሰራራትና ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ስኬት ትልቅ መሰረት የጣለ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ግድቡ በሚሰራበት ወቅት ምንም እንኳን ፈተናው ቢበዛ ከሚፈልገው ግብ እና ከታለመው ህልም ሊያስቀረን የቻለ ምንም አልነበረም ብለዋል፡፡
ፈተናዎች ከሀገር ውስጥ ብቻ አልነበሩም ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከውጪም ብዙ ጫናዎች እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡
አለም በተዛባ መንገድ ጉዳዩን ሲያቀርበው እውነትንና ፍትህአዊነትን ለማስረዳት ከፍተኛ ጥረት መድረጉን ገልፀዋል፡፡
አባይ ያለፈው ትውልድ ብዙ ያንጐራጐረበትና የተቆጨበት ነበር ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በዚህ ትውልድ ዘመን የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ከጉስቁልና በመውጣት ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዝቅተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያዊያን ሣይቀሩ በጋራ ርብርብ በማድረግ አሻራቸውን በግድቡ ላይ ማሳረፍ መቻላቸው በጋራ ስለመቆማችን ምስክር ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ