ተሳፋሪ በመምሰል በተለምዶ ሿሿ ተብሎ የሚጠራ የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ 10 ተጠርጣሪዎች ከነ ተሽከርካሪያቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ግለሰቦቹ ተሳፋሪ በመምሰል የማታለል ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት መስከረም ሦስት ቀን 2018 ዓ/ም በቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ባምቢስ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው መሆኑን ፖሊስ አስታዉቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ኮድ 3-98351 ኦሮ በሆነ ሚኒባስ መነሻቸውን ፒያሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በማድረግ ወደ አውቶብስ ተራ፣ አብነት፣ ጥቁር አንበሳ እና ባምቢስ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ወንጀሉን ሲፈጽሙ እንደነበር ታውቋል።

ግለሰቦቹ ይህንን የማታለል ወንጀል የሚፈጽሙት ተሽከርካሪውን ሞልተው ከተቀመጡ በኋላ አንድ የቀረው በማለት በማስገባትና ትራፊክ መጣ ዝቅ በል፣
አንዴ ውረድ በማለትና በማዋከብ ስልክ፣ ገንዘብ እና የተለያዩ ንብረቶችን እንደሚወስዱ የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከግል ተበዳዮች ለመርማሪ ፖሊስ ከሰጡት ቃል ማረጋገጡን ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ ቀደም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ ሰባት ሲግናል ከሚባል አካባቢ ተመሳሳይ የማታለል ዘዴ ተጠቅመው የአንዲት ግለሰብን ስልኳን እንደወሰዱባት እና የተሽከርካሪውን ሠሌዳ ቁጥር መስጠቷን የጠቆመው ፖሊስ የተሽከርካሪው ሠሌዳ ቁጥር በተለያዩ ክ/ከተሞች ለሚገኙ ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መበተኑን አስታውሷል።
ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ክ/ከተሞች እየተዘዋወሩ የተለመደ የወንጀል ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ከቆዩ በኋላ በቦሌ ክ/ከተማ ባምቢስ አካባቢ በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር አባላት ሊያዙም ችለዋል። ከተገኙባቸው የሞባይል ስልኮች የማረጋገጥ ስራ ሲሰራ አንደኛው የግል ተበዳይ ተጠርጣሪዎቹ በተያዙበት ዕለት አውቶብስ ተራ አካባቢ ስልኩን እና 10 ሺ ብር እንደወሰዱበት አረጋግጧል።
እስካሁን ሁለት የግል ተበዳዮች በተጠርጣሪዎቹ ንብረታቸው እንደተወሰደባቸው ያመለከቱ ሲሆን የአንደኛውን ሞባይል ስልክ ይዘውት እንደተገኙም ፖሊስ ጠቅሷል።
በአጠቃላይም 10 ተጠርጣሪዎች ከነተሽከርካሪያቸውና 4 ስማርት ስልኮችን በመያዝ ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።