AMN – መስከረም 5/2018 ዓ/ም
በዓለም ላይ ስመ ገናና እና ሃያላን ሃገራት እዚህ ለመደረሳቸው ሚስጥሩ ዘመኑ የሚፈለገውን በትምህርት የዳበረ በቂና ብቁ ዜጋ ማፍራት መቻላቸው ነው፡፡ ታዲያ በትምህርት ቤት የሚሰጡ የቀለም ትምህርቶች በተማሪዎች ላይ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ለማድረግ የሥነ ልቦና ዝግጅት ላይ ቀድሞ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ ዜጋ ለማፍራት የትምህርት ሴክተሩን ሪፎርም ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመስራት በዙ ርቀት ተጉዛለች ማለት ይቻላል፡፡
የ2017 የትምህርት ዘመን ተጠናቆ ተማሪዎች እና መምህራን በዕረፍት፣ በስልጠና አና በተለያዩ ሁኔታዎች ከመማር ማስተማሩ ርቀው ቆይተዋል፡፡ ከሁለት ወር የእረፍት ጊዜያቸው መልስም ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ ተጀምሯል፡፡
ታዲያ በዕረፍት ያሳለፈን አዕምሮ ወደ ትምህርት ለመመለስ የሚኖረው የስነ-ልቦና ዝግጅት ምን ሊሆን ይገባዋል ስንል ጠቅላላ ሃኪም እና የአዕምሮ ህክምና ባለሞያ የሆኑትን ዶክተር አቤል ግርማን ጠይቀናቸዋል፡፡

ተማሪዎች፣ መምህራን እና ትምህርት ቤቶች በዕረፍት ላይ መቆየታቸው፤ ትምህርት ቤቶች ለአዲስ ዓመት የትምህርት ግብአቶችን ለማሟላት፣ ለእድሳት እና ለአዲስ ዓመት የትምህርት ዘመን ዝግጅት፤ መምህራን በተለያዩ ስልጠናዎችና ሌሎች ጉዳዮችን ለመከወን እድል እንዲያገኙ ሲያደርግ፤ ለተማሪዎች ደግሞ ሰፊ የመዝናኛ ጊዜ የሚሰጥ በመሆኑ አዲሱን የትምህርት ዘመን በጉጉት እና በተስፋ እንዲጠበቁ ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ዶክተር አቤል ነግረውናል፡፡
ነገር ግን ዕረፍት ተጠናቆ ወደ መደበኛ ትምህርት በመመለስ ሂደት ውስጥ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በተማሪዎች ላይ ለየት ያሉ ስነ-ልቦናዊ ክስተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያሉት ባለሞያው፤ በተለይ በአዲስ ክፍል የመማር፣ የመምህራን ለውጥ፣ ከአዳዲስ ተማሪዎች ጋር መቀላቀል፣ የአዲስ የትምህርት ዓይነት እና የትምህርት ቤት ለውጥ ሲኖር በተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አንስተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሶስት አካላት ስራ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር አቤል፤ ወላጆች ትምህረት ሲጀመር ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት ባሻገር በትምህርት ቤት በመገኘት የመማሪያ ክፍሎቻቸውን መመልከት፣ ከክፍል ጓደኞቻቸው ጋር መተዋወቅ፣ ከመመህራኖቻቸው ጋር መገናኘት እና ስለልጆቻቸው የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ችግሮችን ማቃለል እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

በመምህራን ደረጃ የበርካታ ተማሪዎችን ባህሪ እና ፀባይ አቻችሎ ስራዎችን የሚያከናውኑ ቢሆንም፤ ተማሪዎቹ በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አዳዲስ የማስተማር ዘዴዎችን መተግበር፣ በተማሪዎች ለሚስተዋሉ አዳዲስ ፀባይ እና ክስተቶች በቅንነት የሚፈታና የሚረዳ ለመሆን ራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡
ተማሪና መምህራንን የሚያገኛው ተቋም ትምህርት ቤት ነው ያሉት ባለሙያው፤ ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያ የትምህርት ማስጀመሪያ ሳምንት ተማሪዎች እና ቤተሰቦች የትምህርት ቤቱን አዳዲስ ስራዎችና ለውጦች እንዲጎበኙ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ቀልብ ለመግዛት ልዩ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ዝግጅቶችን በማከናወን እና የትምህርት ቤታቸውን ቆይታ አሰልች እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአጠቅላይ ተማሪዎች የትምህርት መጀመሪያ ሳምንታት ላይ የተነቃቃ እና በቀጣይ ለሚሰጠው መደበኛ ትምህርት በስነ-ልቦና የተዘጋጁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ ባለሞያው ዶክተር አቤል ግርማ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በያለው ጌታነህ