የትራምፕ አስተዳደር እና ቻይና ቲክቶክ በአሜሪካ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሁለቱ መንግስታት የማዕቀፍ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እንዲሁም የቻይና እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በመጪው አርብ በሚኖራቸው ግንኙነት ስምምነቱን እንደሚያጸድቁት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሃላፊ ስኮት ቤሴንት ይፋ አድርገዋል።
ሃላፊው አክለውም የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም እና የቻይናን ፍላጎት ያማከለ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለፁት።
የቻይና እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በዚህ ሳምንት በስፔን ማድሪድ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት የተመለከተ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የአሜሪካውያንን የግል ሚስጥር ለቻይና መንግስት አሳልፎ ይሰጣል በሚል በቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቀረበበት ክስ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የከረመው ቲክቶክ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ፍቃድ አግኝቷል።
ለአንድ አመት በቆየው ውዝግብ የባይትዳንስ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ጥቂት አክሲዮኑን ለአሜሪካውያን ድርጅቶች ወይም ባለሀብቶች እንዲሸጥ ቅድመ ሁኔታ ቀርቦለት እንደነበር ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ቲክቶክ በአሜሪካ መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ድርሻውን ለአሜሪካ ኩባንያ ለመሸጥ ፈቃደኛ ያልነበረው የቻይናው ባይትዳንስ በዚህ ጉዳይ መስማማት እና አለመስማማቱ ላይ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።
ከንግድ ድርድሩ በኋላ የወጡ መረጃዎች ሁለቱ ሀገራት በቲክቶክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ መቀጠል ዙሪያ የደረሱበትን ዝርዝር ነጥቦች አልገለጹም።
በአሁኑ ወቅት ቲክቶክ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ1.5 ቢሊየን በላይ ወርሀዊ ተጠቃሚዎች ሲኖሩት ፤ በአሜሪካ ድግሞ ከ136 ሚሊየን -170 ሚሊየን ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዳዊት በሪሁን