የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጰያ የቁልቁለት ጉዞ ያበቃበት የብልጽግና ጉዞ ዳግም ጅማሮ ማሳያ መሆኑን የባህዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳለማው ገልፀዋል።
በአማራ ክልል የታላቁን የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አሰመልክቶ ባህርዳር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የድጋፍ ሰልፎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአማራ ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አብዱ ሁሴን፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአባት አርበኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው የህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት የግጭት የኋላ ቀርነት ምሳሌ ተደርጋ የመወሰዷን ታሪክ ለመቀየር ልጆቿ አርቀው ተመልክው በትልቁ አስበው ወደ ክብሯ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል።
ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም በይፋ የተመረቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የቁልቁለት ጉዞ ያበቃ መሆኑን ያስረዱት አቶ ጎሹ ፣ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ዳግም መጀመሩን ማሳያ ነው ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የታሪክ እጥፋት ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው፤ የኢትዮጵያውያን ያአሸናፊነት እና የአይበገሬነት ታሪክ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በሔለን ተስፋዬ