AMN – መስከረም 6/2018 ዓ/ም
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከፈለው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንደ አድዋ ሁሉ የዘመኑ ህያው መገለጫችን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፈጣሪ የተቸራትን አንጡራ ሃብት የራሷን ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጐልበት ተጠቅማ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባቷ ለአፍሪካዊያን ትልቅ ምሳሌ እና ኩራት ነው ብለዋል፡፡
ይህ አንፀባራቂ ስኬት ቀደምት አባቶቻችን እንዳወረሱን የአድዋ ድል ሁሉ ለመላ ጥቁር ህዝቦች በተለይም ደግሞ በድህነት ለሚማቅቁ አፍሪካዊያን ሃብታቸውን ተጠቅመው በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶቿን በአለም አደባባይ ሞግታ፤ የራሷን አንጡራ ሀብት በራሷ የግዛት ወሰን ያለማንም ዕርዳታና ድጋፍ በራሷ አቅም በይቻላልና በአይበገሪነት መንፈስ በመስራቷ በአለም አደባባይ ጐልታ እንድትታይ አድርጓታል፡፡፡

ግድቡ ኢትዮጵያዊያን እንደ አድዋ ድል ሁሉ ለሀገራዊ ክብርና ጥቅም ሲሉ ልዩነታቸውን ወደ ጐን ትተው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜቸውን ሠውተው የገነቡት ሲሆን፤ ይህም ለታሪክና ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ ሀገራትና ቅኝ ገዥዎቻቸውን መሰሪ የሥምምነት ውልን እስነከመዘዙ ያከሸፈ ነውም ብለዋል፡፡
ግድቡ በየገጠሩ በጪስ ለሚሰቃዩ ወገኖቻችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮና የጤና ሁኔታቸው እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ የውጪ ምንዛሬ ገቢንም የሚያሳድግ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም አፍሪካዊያንን በተለይም ደግሞ ጐረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያሳልጥ ነው ብለዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው