በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች በብዛት የሚጸጸቱባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

You are currently viewing በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች በብዛት የሚጸጸቱባቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

AMN – መስከረም 6/2018 ዓ/ም

የሚሞትበትን ጊዜ የማያውቀው የሰው ልጅ በምድር ላይ ማድረግ እና ማሳካት የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሲያሳድድ የእድሜው ማምሺያ ላይ ይደርስ እና ወደ ሞት ይጓዛል፡፡

ታዲያ በዚህ ጊዜ አንዳንዶች በዘመናቸው ይጠቅመኛል ብለው ትኩረት የሰጡት ነገር እንዳሰቡት ደስታን ሳያስገኘላቸው ሲቀር አልያም ማድረግ ሲኖርባቸው ባላደረጉት ነገር በመጨረሻው ሰዓት ይጸጸታሉ፡፡

ሚረር ጋዜጣ በጽኑ ታመው ለረጅም ጊዜ በሆስፒታሎች ውስጥ የሚተኙ ታማሚዎችን የሚያክሙ ሀኪሞችን እና ተንከባካቢዎችን አነጋግሮ በሰራው ዘገባ በብዛት የሰዎች ጸጸት ሕይወትን በሚዛን ካለመምራት እንደሚመነጭ አስነብቧል። በጠና ታመው ለረጅም ጊዜ በአልጋ ላይ የዋሉ ሰዎችን የሚያስታምሙ ሀኪሞች ከልምዳቸው የሰዎች የጸጸት መነሻ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አጋርተዋል።

ሀኪሞቹ ሰዎች ወደ ሞት በተጠጉ ቁጥር ነገን ማሰብ አቁመው ዛሬ እና ትላንት ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚያደርጉ፤ በዚህ ወቅት በብዛት አምልጦኛል በሚሉት ጊዜ ስላላደረጉት ወይም ስላደረጉት ነገር እያነሱ ጸጸታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ ነገ የሚባል ነገር የለም የሚሉት ሀኪሞቹ፤ እድል ቢያገኙ ማስተካከል የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ብቻ ይበልጥ እንደሚያስጨንቋቸው ይገልጻሉ፡፡

በርካታ ሰዎች በእስትንፋሳቸው መጨረሻ በብዛት የሚጸጸቱባቸው ነገሮች በሚል ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል ቀዳሚው ከቤተሰብ እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በቂ ጊዜ አለማሳለፍ ነው፡፡ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸው በሚመስሉ ቁሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር ለቤተሰብ ፣ ለሚስት ፣ ለባል ፣ ለልጅ እና ለሌሎችም የቅርብ ሰዎች በቂ ጊዜ አለመሰጠት ሰዎች ከሚጸጸቱባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ሆኗል፡፡

ሌላው በስራ ላይ የሚጠፋ ሰፊ ጊዜ ነው። ነገን የተሻለ ለማድረግ እና ሕይወትን ለመምራት ሰዎች በስራቸው ውስጥ ጠልቀው መግባታቸው ህይወት የምታቀርባቸውን ሌሎች ስጦታዎች እንዳይመለከቱ፤ ህይወታቸው በሙሉ ከስራ ጋር ብቻ የተቆራኘ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

በዚህም ከሰዎች ጋር ይበልጥ እንዳይገናኙ ፣ በበዓላት እና ማህበረሰባዊ መሰባሰቦች ላይ እንዳይሳተፉ ፣ ሌሎች ሀገራትን እንዳይጎበኙ እና በጥቅሉ ሕይወትን በቅጡ እንዳያጣጥሙ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል በስራ ላይ ከመጠን በላይ ጊዜን ማጥፋት ይጠቀሳል፡፡ ዛሬን አለመኖር የሰዎች የጸጸት ምንጭ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱ ነጥቦች መካከል እንዱ ነው፡፡

በእቅድ እና በሃላፊነት መመራት፣ መጪውን ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ተገቢ ቢሆንም ነገ ላይ በማተኮር በእጅ ላይ ያለ ዛሬን ማጣት ደግሞ ለጸጸት ይዳርጋል ነው የተባለው፡፡ ገና ባልጨበጥነው የነገ ሁኔታ ላይ ከመጠን በላይ ከመጨናነቅ ይልቅ በእጃችን ላይ በሚገኘው ዛሬ ቁምነገር መስራት እና ደስተኛ ሆነን ማሳለፍ ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ሀኪሞቹ መክረዋል፡፡

በስተመጨረሻም የሰዎች ጸጸት የሚመነጨው በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስናደርግ፣ ሌላውን በመዘንጋት፣ በጥቅሉ ህይወትን በሚዛን ካለመምራት የሚነሳ በመሆኑ ለሁሉም እንደየመጠኑ አስፈላጊውን ትኩረት እና ጊዜ በመስጠት ከጸጸት የጸዳ ህይወትን ለመምራት ያስችላል ተብሏል፡፡

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review