በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ሚኪሊላንድ ኮንደምንየም ተብሎ በሚጠራው እና በአካባቢው ያጋጠመ የመሬት መሰንጠቅ ነዋሪዎችን የአደጋ ስጋት ላይ እንዳይጥል የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን በም/ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለፁ።
ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ይህን የገለፁት በትናንትናው እለት መስከረም 5/ 2018 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሚኪሊላንድ ኮንደምንዬም፣ ሚኪሊላንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም በወረዳ 14 የሚገኝ ቤተ እምነትና አካባቢው ከክረምቱ ማገባደጃ ወራት ጀምሮ ያጋጠመ የመሬት መሰንጠቅ ተባብሶ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የተሰሩ የቅድመ አደጋ ጥንቃቄዎችን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ነው።
ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት ምንም እንኳን የመሬት መሰንጠቅና መሰል የአደጋ ስጋት ከዚህ ቀደም በዚህ ቦታና አካባቢ ተከስቶ ባያውቅም ከአንድ ወር ወዲህ ግን በአካባቢው ይህን መሰል ስጋት መኖሩ መረጃ እንደተገኘ የከተማ አስተዳደሩ በአፋጣኝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጅ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር ጥናት እንዲካሄድ ተደርጓል፣የጥናቱን ውጤትም በዛሬው እለት ይፋ ይደረጋል ሲሉ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ምንም እንኳን የአደጋ ስጋቱ መኖሩ ከታወቀ አጭር ጊዜ ቢሆንም ባለፉት ቀናት በሚኪላንድ ኮንደምንዬም ብሎክ 13 ነዋሪዎች የሆኑ 29 አባዎራዎች ማለትም150 በላይ የቤተሰብ አባላትን ከአደጋ ስጋት ነፃ ለማድረግ ከነበሩበት ቦታ የማራቅ ስራ መሠራቱንም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ሃላፊዎችም አመላክተዋል፡፡