ብቁና ተወዳዳሪ የፈጠራ ክህሎት ያለው የሰለጠነ ባለሙያ በማፍራት ለመዲናዋ ፈጣን የለውጥ ጉዞ የድርሻውን ሃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ለሚ ኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ አስታውቋል።
ለሚ ኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የስያሜ ለውጥና የ10ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን አክብሯል።
2007 ዓ.ም ቦሌ ህዳሴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በሚል ስያሜ የተቋቋመው የአሁኑ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ፤ ላለፉት አስር ዓመታት በተለያዩ የስልጠና መስኮች ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ኮሌጁ ውጤት ተኮር ስልጠናዎችን በመስጠት ብቁ፣ ተወዳዳሪና በፈጠራ ክህሎት የዳበረ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት አይናለም ተናግረዋል።
የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ዲን ታደሰ መኮነን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኮሌጁ ባለፉት 10 ዓመታት ገበያ መር የሆነ ውጤት ተኮር ስልጠና በመስጠት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እንዳፈራ ገልፀዋል።
ኮሌጁ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት ጎን ለጎን በተለይም የኢንተርፕራይዞችን ችግር የሚቀርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በየአመቱ በመቅዳትና በማላመድ የበርካቶችን ችግሮች እያቃለሉ እንደሚገኙ ታደሰ መኮነን (ደ/ር) ተናግረዋል።
ኮሌጁ ለሚቀጥሉት አስር አመታት ስትራቴጂክ ግብ በማስቀመጥ ወደ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለማሸጋጋር እና የቅበላ አቅሙን ማሳደግ የሚያስችሉ እንዲሁም የውስጥ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በእቅድ ማስቀመጡ ተገልጿል።
በታምሩ ደምሴ