የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር እንዳሉት የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚያሰድንቅ ሁኔታ ተጠናቆ በማየታቸው ላቀ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፤ ግድቡ የተባበሩ ክንዶች ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያን ትልቅነት እና ከዚህ የተሻገረ ስራን መስራት እደምትችል የመሰከረ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ግድቡ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ ለመጠናቀቅ የበቃ ነው ያሉት አፈ-ጉባዔዋ፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያ አሻራ ደምቆ የታየበት ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጥራር አባይ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውን ስጦታ እና ሀብት ሆኗል በዚህም ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡
የልማት ስራው የኢትዮጵያን ትልቅነት ለዓለም ያሳየንበት ነው ያሉት ኃላፊው የኢትዮጵያውያንን መቻል ማረጋገጫ ማህተም መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በስፍራው የተከናወነው የልማት ስራ ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ሂደት የላቀ አበርክቶ እደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ስፍራ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ታሪክ ነው የተሰራው ሲሉም አክለዋል፡፡ በዚህ ትውልድ ተገንብቶ እና ተጠናቆ ማየት ከፍተኛ ደስታ ይፈጥራል ያሉት አቶ ጃጥራር ይህ ለኢትዮጵያውያ ትልቅ ኩራት ነው፤ የትውልዱ ዓድዋ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡