ስም ከስያሜነቱ ተሻግሮ የሰዎች ባህሪ እና ማንነት መገለጫ ጭምር እንደሆነ ይታመናል።
በአለም ላይ በሚገኙ የተለያየ ሀገራት ህዝቦች ስሞችን ከባህል ፣ ከስነልቦና ፣ ከሀይማኖት እና ከሌሎችም ማህበረሰባዊ መገለጫዎች በመቅዳት ስያሜዎችን ያወጣሉ። ስምን መልአክ ያወጣዋል የሚል ብሂል ያላቸው ኢትዮጵያውያንም በብዛት ስሞችን ከባህል እና ከሀይማኖት በመነሳት ይሰይማሉ።
ባለፉት ቅርብ አመታት መሀመድ የሚለው ስም በአለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ ሀገራት ቀዳሚ ተመራጭ ስም ስለመሆኑ የተለያዩ ዘገባዎች ወጥተዋል። የብሪታንያ ብሔራዊ መረጃ ማዕከል ባወጣው መረጃ በፈረንጆቹ 2023 ዓመት ከተወለዱ አጠቃይ ህጻናት ውስጥ መሀመድ የሚለው ስም የተሰጣቸው ህጻናት ቁጥር ከፍተኛው ሆኖ መገኘቱን አመላክቷል።
በተመሳሳይ በ2025 በእስራኤል ለህጻናት ከሚወጡ ስሞች መካከል መሀመድ የሚለው ስም 3ኛ ደረጃን ይዟል። ወርልድ ፖፕሌሽን የፈረንጆቹን 2025 እና ከዛ በፊት በነበሩ ተከታታይ አመታት በአለም አቀፍ ደረጃ በብዛት ጥቅም ላይ የዋሉ ስሞችን እና ሀገራት ዝርዝርን ይፋ አድርጓል።
የአፍሪካ አህጉር በርካታ ባህል እና ሀይማኖት መገኛ እንደመሆኑ ስያሜዎችም እንደየአካባቢው እንደሚለያይ የገለጸው ሪፖርቱ፤ ለአብነት በናይጄሪያ- ኢብራሂም ፣ በአልጄሪያ- ሳኢዲ ፣ በደቡብ አፍሪካ- ኒኮሲ ፣ በሶማሊያ- አሊ የሚባሉ ስሞች እንደሚበረክቱ አስነብቧል። መሀመድ ፣ እና ስሚዝ የተሰኙት ስሞች ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ በብዛት ጥቅም ላይ የዋሉ ናቸው በሚል ተለይተዋል።
ከዚህ ባለፈ በአርጄንቲና – ጎንዛሌዝ ፣ አውስትራሊያ – ስሚዝ ፣ ባንግላዲሽ – አክቴር የሚሉ ሰዎች የሚዘወተሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ተስፋየ የሚለው ስም በብዛት ጥቅም ላይ እንደሚውል ሪፖርቱ አመላክቷል።
በዳዊት በሪሁን