AMN መስከረም 6/2018
ትምህርት ሚኒስቴር የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሃገር አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው የወንድ ተማሪዎች ውጤት ከዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ ት/ቤት 591 መሆኑን እና በሴት ተማሪዎች ከብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት 579 ሆኖ መመዝገቡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ተማሪ ካሊድ በሽር ከዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ ት/ቤት 591 አጠቃላይ ዉጤት ማምጣቱን እንዲሁም በሴት ተማሪዎች ተማሪ ሃይማኖት ዮሃንስ ከአዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ት/ቤት 579 ማምጣቷን መዘገባችን ይታወሳል። ይሁን እንጂ የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ ት/ቤት ተፈታኝ የሆነችው ተማሪ ገነት መርጋ ጊሹ 579 አጠቃላይ ውጤት በማምጣት ቀዳሚ መሆኗ መረጃ ደርሶናል።

ይህንኑ መረጃ መሠረት በማድረግ የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑትን አቶ ዴቱ ዲቦራን አነጋግረናል። ርዕሰ መምህሩም ተማሪ ገነት መርጋ ጊሹ 579 አጠቃላይ ውጤት ማምጣቷን አረጋግጠውልናል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ተማሪዎች ተመሳሳይ ነጥብ ስላመጡ ለሁለቱም ተማሪዎች እውቅና መስጠት እንሰነበረበት የተናገሩት ርዕሰ መምህሩ ይህንኑ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ማሳወቃቸውን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል። ይስተካከላል ጠብቁ’ የሚል ምላሽ እንዳገኙም አቶ ዴቱ ተናግረዋል።
ኤ ኤም ኤን ዲጂታል የተማሪ ገነት መርጋ ጊሹ አጠቃላይ ውጤት 579 መሆኑን ባገኘዉ መረጃ አረጋግጧል። ተፈታኟ በሂሳብ ትምህርት 100: በፊዚክስ 100: በባዮሎጂ 98: በእንግሊዝኛ ቋንቋ 95 : በኬሚስትሪ 93 እንዲሁም አፕቲትዩድ 93 ማስመዝገቧን አረጋግጧል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮና ከትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ የምንገኝ መሆኑን እየገለጽን ምላሻቸዉ እንደደረሰን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን።
በመልካሙ አበበ