ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን መጻዒ እጣፈንታ ብሩህ ያደረገ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን መጻዒ እጣፈንታ ብሩህ ያደረገ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ

AMN – መስከረም 7/2018 ዓ.ም

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን መጻዒ እጣፈንታ ብሩህ ያደረገ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ በጉባ በመገኘት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የጎበኙ ሲሆን በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጥ፤ ለዘመናት ቁጭት ምላሽ የሰጠ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከዚህ በላይ የሚያኮራ እና ልብን የሚያሞቅ ተግባር የለም ያሉት ኃላፊው፣ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ከሃይል ማመንጨት በላይ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የዘመናት ቁዘማን ያስወገደ እና ኢትዮጵያውያን በዓለም አደባባይ በኩራት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገር እድገት እና ብልጽግና መሰረት ሊሆን የሚችል ግዙፍ ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፣ የጀግንነት እና ብሄራዊ ኩራት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል የትውልድ ስጦታ ነው ብለዋል፡፡

በበልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምጸሃይ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ ያስቻለ ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል፡፡

በህብረት መቻል፣ ችሎም ማሳየት የህዳሴ ግድብ መገለጫ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ መስራት እና ታሪክ ማስመዝገብ እንደምንችል ያሳየንበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዘመናት የቁጭት ጉዞ ማብቂያን እውን ያደረግንበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የመቻል አቅማችን የታየበት ታላቅ ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ እና በአንድ ሲቆሙ የትኛውንም ችግር ድል ማድረግ እንደሚችሉ የታየበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ደቻሳ ፕሮጀክቱ በብዙ ችግር ውስጥ አልፎ ለፍጻሜ በመብቃቱ ላቅ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው የልማት ስራው የዘመናት የትውልድ ጥያቄን የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review