የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ታሪክ ሰሪዎች እንጂ ዘካሪዎች አንሆንም በሚል መነሳሳት የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር እሳቤ የጻፉት 4ኛው መጽሃፍ ”የመደመር መንግሥት” መስከረም 6 ቀን 2018 ዓ. ም ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፅሐፍት ምርቃት ወቅት እንደተናገሩት፤ የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ”መነሻ”፣ ”መዳረሻ”፣ ”መንገድ” እና ”መንግሥት” በተሰኙ አራት ሃሳቦች ወይም ዙሪያ እንደሚያጠነጥን አብራርተዋል። ከዚህም በመነሳት መጽሃፉ ኢትዮጵያ ለምን ደሃ ሆነች ከሚል ቁጭት እንደሚነሳ ጠቁመዋል።

ለዚህም መፅሃፉ የመፍትሄ ሃሳብን አስቀምጧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መፍትሄዎቹም የኢትዮጵያን መዳረሻ በግልጽ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚመኝ ብቻ ሳይሆን እንዲሳካ የሚሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት ስራ ሳይሰራ ጊዜ ካለፈ በኋላ ምክንያት ለመደርደር የተዘጋጀ መፅሐፍ እንዳልሆነ ገልፀው፤ በተሰጠን ጊዜ እና ዘመን ታሪክ የምንሰራ እንጂ ዘካሪዎች አንሆንም በሚል መነሳሳት የተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሔለን ተስፋዬ