‎ያጋጠመው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ መንስኤ በአካባቢው ተገቢ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ

You are currently viewing ‎ያጋጠመው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ መንስኤ በአካባቢው ተገቢ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ ባለመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ

AMN – መስከረም 7/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ሚኪሊላንድ ኮንዶምንየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያጋጠመው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ መንስኤ ተገቢ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ ባለመኖሩ ምክንያት መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በነሀሴ ወር 2017 ዓ.ም ከባድ ዝናብ መጣል መጀመሩን ተከትሎ የተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ፣ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት ኢንጅነር ወንድሙ፣ የመሰንጠቅ ምልክቱ አካበቢ የሚገኙ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎችን በጊዜያዊነት ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከጊዜያዊነት መፍትሄው ባሻገር የአደጋውን ትክክለኛ መንስኤ ለማወቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ ሳይንስ ምሁራን አካባቢው ድረስ በመሄድ ጥናት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ጥናት አድርጎ ባቀረበው ውጤት መሰረት፤ የመሰንጠቅ ምልክት የታየበት አካባቢ፣ ኮንዶሚንየሞቹ ሲገነቡ ምልስ አፈርን ጨምሮ በርካታ የኮንስትራክሽን ተረፈ ምርቶቸ የተደፉበት ቦታ እንደሆነ መረጋገጡን ኢንጅነር ወንድሙ ተናግረዋል ፡፡

በኮንዶሚኒየሞች አካባቢ የሚገኙ የጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦዎች አብዛኛዎቹ በአረምና በቆሻሻ የተደፈኑ በመሆናቸው የሚወርደው የዝናብ ውሃ ወደ መሬት ውስጥ በመስረግ እና አፈሩን በማላላቱ ምክንያት መሬቱ የመሰንጠቅ፣ የመስመጥና የመንሸራተት ሁኔታ እንደተፈጠረ በጥናቱ ውጤት ተጠቁሟል ብለዋል፡፡

የተከሰተውን የመሬት መሰንጠቅ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል በአካባቢው የሚመጣውን ውሃ ወይም ጎርፍ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ትክክለኛ የተፋሰስ ቦታ መልቀቅ እና ዛፎችን በአካባቢው መትከል የሚገባ እንደሆነ በጥናቱ መመላከቱን ሃላፊው ገልፀዋል ፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review