በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የተወለደው ተማሪ ካሊድ በሽር፣ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በካቶሊክ የህፃናት ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ 4ኛ ክፍል ከ2ኛ ሴሚስተር ጀምሮ ደግሞ በጎባ ከተማ በሚገኘው 1ኛ ደረጃ ነው ትምህርቱን የተከታተለው፡፡
እሰከ 8ኛ ክፍል ድረስ በዚሁ ከተማ የተማረ ሲሆን የታዳጊውን ትምህርት የመቅሰም አቅም የተገነዘቡት መምህሮቹ እጅግ ያበረታቱት እንደነበር ይናገራል፡፡ በርግጥ ታላቅ እህቴ እና ወንድሜም በትምህርታቸው ጎበዝ የሚባሉ ስለነበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር ብሏል፡፡ ወላጆቼም የተማሩ በመሆናቸው በልጅነት ዕድሜዬ በጫዎታ ጊዜየን በከንቱ እንዳላጠፋ እና እንዳልዘናጋ ክተትል ያደርጉ እንደነበርም አስታውሳለሁ ይላል፡፡

በ2014 ዓ.ም 8ኛ ክፍል ላይ በባሌ ዞን ከፍተኛ ውጤት ማምጣት በመቻሌ የዶዶላ ኢፈ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መቀላቀል ችያለሁ ይላል፡፡ ከቤት ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ያሉ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ስለያዙኝ እኔም ከመዋለ ህፃናት ጀምሮ ጥሩ ውጤት እያስመዘገብኩ ለዛሬ ደርሻለሁ ሲል ጎበዙ ካሊድ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም በ2017 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከ600 ዘጠኝ ብቻ በማጣት በ591 ነጥብ በኢትዮጵያ የዓመቱ ከፍተኛ ውጡት ያስመዘገበ ተማሪ ሊሆን ችሏል፡፡
ካሊድ ፊዝክስ እና ሂሳብ የመሰሉ የትምህርት ዓይነቶችን መቶ ከመቶ ነው ያስመዘገበው፡፡ እንግሊዘኛ 96 ከመቶ፣ ኬሚስትሪ እና አፕቲትዩድ 98 ከመቶ እንዲሁም ባዮሎጂ 99 ከመቶ አግኝቷል፡፡ ይህን ውጤት ለማምት የተለየ ነገር የለውም፤ ጠንክሮ መሥራት ብቻ ነው፣ በርትቼ ስላጠናሁ እና በአግባቡ ትምህርቴን በመከታተሌ ጥሩ ውጤት አስመዝግቤያለሁ ብሏል፤ የ2017 ዓ.ም ብሔራዊ ፈተና ጀግናው ተማሪ ካሊድ በሽር፡፡
ለካሊድ አርአያ የሆነው ታላቅ ወንድሙ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜዲካል ዶክተር ሲሆን፣ እህቱ ደግሞ በኢንፎርሜሽን ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዛለች፡፡ የካሊድ የወደፊት መሻት የሶፍት ዌር ኢንጅነር መሆን ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ተምሬ ሀገሬን እና ህዝብን ለማገልገል ትልቅ ተስፋ ሰንቄያለሁም ይላል፡፡ ጥሩ የትምህርት ዕድል ቢመቻችለት ደግም ይህን ማሳካት ቀላል እንደሚሆን እምነቱን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ደስታ ላይ ባለሁበት ወቅት አባቴ ከአንድ ወር በፊት የደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ደስታዬን ሙሉ እንዳይሆን አድርታል ይላል ካሊድ፡፡ ብዙ ቦታ ለህክምና ብንወስደውም የተሻለ ህክምና እንደሚያስፈልገው ነው የተነገረን፡፡ አቅም ያላችሁ ሰዎች አግዙኝ ደስታዬም ሙሉ ይሁን ብሏል የዘንድሮ ብሔራዊ ፈተና ቁንጮ ተማሪ ካሊድ በሽር፡፡
እናቱም ልጄ ከትምህርት ቤት እና ከመስጊድ ውጭ እምብዛም በጫወታ ጊዜውን አያጠፋም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አጎቱ ሀጂ ጀማል ሀሰን በበኩላቸው፣ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረው፣ አባቱም የህክምና ድጋፍ ቢደረግለት ጥሩ ነበር ብለዋል፡፡
ካሊድ ተማሪዬ ነበር ያለው መምህር ሽመልስ ጢቆ ደግሞ ምስጉን እና ልዩ ተማሪ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ ውጤት ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም ነው ያለው፡፡ ካሊድ፣ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ቢመቻችለት ህልሙን አሳክቶ እራሱንም ሀገሩንም እነደሚጠቅም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በማሬ ቃጦ