ተማሪ አሉዲን ሁሴን የበደሌ ኢፈ ቦሩ አዳሪ ትምህርት ቤት ታታሪ ተማሪ ነው።
የ12ኛ ከፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመፈተን ዝግጅቱን አጠናቆ የመፈተኛ ቀኑ ሲደርስ ሕመም ያጋጥመዋል ። ተማሪ አሉዲን ህክምና ሂዶ ምርመራ ሲያደርግ የትርፍ አንጀት እንዳለበት በሀኪም ይነገረዋል።
በዚህ አጋጣሚ ጭንቀት ውስጥ የገባው አሉዲን ሕመሙ ፈተናውን መጨረስ የሚያስችልበት ደረጃ ላይ በመሆኑ ት/ቤቱ ከሀኪሞች ጋር በመነጋገር መድኃኒት እየወሰደ እንዲፈተን መደረጉን የት/ቤቱ ር/መምህር አቶ ይልማ ገቢሳ የነበረውን ተናግረዋል። ህክምና እየተደረገለት ለ3 ቀን ሲሰጥ የነበረውን የማሕበራዊ ሳይንስ ፈተና ያጠናቀቀው ይህ ጎበዝ ተማሪ 472 ማምጣት ችሏል።
በወቅቱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በበደሌ ኢፈ ቦሩ ትምህርት ቤት እየተሰጠ ያለውን የፈተና ሂደት በጎበኙበት ወቅት ፣ ተማሪውን አበረታትተው እና መልካሙን ሁሉ ተመኝተው ነበር።
ሃገር የምትገነባው ፣ ችግርን ተቋቁመው ዓላማቸውን ለማሳካት በሚጥሩ እንደ አሉዲን ባሉ ብርቱ ዜጎች ጥረት ነው ማለታቸዉን ከጅማ ዩኒቨርስቲ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።