ማንችስተር ዩናይትድ ለደጋፊዎቹ እንደቀደመው ጊዜ ደስታን ሳይሆን ቁዘማን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከለቀቁ በኋላ ክለቡ እያሽቆለቆለ ያለበት ፍጥነት ያስደነግጣል፡፡
ደግሞ ደጋግሞ ዋንጫ ያሸነፈው ክለብ በቅጡ መፎካከር አቅቶት በማይጠበቁ ክለቦች ጭምር እየተሸነፈ ይገኛል፡፡ በዚህ በጨለማውም ጊዜ ግን ክለቡን ከልብ የሚደግፉ በርካታ ናቸው፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ ኦልድትራፎርድ ከሚታደሙት ጀምሮ በመላው ዓለም በሚገኙ ተከታዮቹ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የሚደገፍ ክለብ ነው፡፡
ከእነዚህ ደጋፊዎች አንዱ የሆነው ፍራንክ ኢሌት እንደዋዛ የገባው ቃል መነጋገሪያ አድርጎታል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ 5 ተከታታይ ጨዋታ ካላሸነፈ ፀጉሬን አልቆረጥም ማለቱ መጀመሪያ ላይ የተለየ ትኩረት አላገኘም ነበር፡፡ ኑሮውን በስፔን ያደረገው የ29 ዓመቱ እንግሊዛዊ የዩናይትድ ውጤት ማጣት ሲከፋ ፣ እርሱም በየቀኑ የፀጉሩን እድገት በኢንስታግራም ገፁ ሲያጋራ የበለጠ እውቅና አግኝቷል፡፡
አሁን ፍራንክ በማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ዘንድ እውቅናው ከፍ ብሏል፡፡ የኢንስታግራም ገፁ ተከታዮችም 330 ሺ አልፈዋል፡፡ ጥቅምት 2024 ላይ የገባውን ፀጉር ያለመቆረጥ ቃል ያስቀጠለው ፍራንክ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል፡፡ ፀጉሩም ጎፍሮ ገፅታውን እስከመቀየር ደርሷል፡፡
ፍራንክ ቃሉን መቼም እንደማያጥፍ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡ በቡድኑ ተስፋ መቁረጥ ለእርሱ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ’’ቡድኑ ጥሩ ውጤት እያመጣ ስላልነበረ መጀመሪያ ደጋፊዎች ለማዝናናት የፈጠርኩት ነበር፡፡ ይህን ያህል ጊዜ ይፈጃል ብዬ ግን አልጠበቅኩም፡፡’’ ሲል ተናግሯል፡፡
ከኢንስታግራም ተከታዮቹ ጋር ቤተሰባዊ ስሜት ፈጥሬያለሁ የሚለው ፍራንክ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የኢንስታግራም ገፁ ተከታዮችን ለበጎ ምግባር እያነሳሳ ይገኛል፡፡ ቃሉ ሲፈፀም የተቆረጠውን ፀጉር ዘ ሊትል ፕሪንሰስ ትረስት (The Little Princess Trust) ለተሰኘው ካንሰር ላይ ለሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለመለገስ ቃል ገብቷል፡፡ ጥያቄው ግን መቼ ነው ይሄ የሚፈፀመው? የሚል ነው፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ