የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ ማቋቋሚያ መድረክ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
በጉባኤው የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለፁት፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥን እርካታ ለመጨመር የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ጃንጥራር አክለውም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ መቋቋም የአምራች ኢንዱስትሪያሊስቱን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም፣ ግልፅና ፈጣን አገልግሎት ከመስጠትም ባሻገር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲቻል መሆኑን ገልፀዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ መቋቋም ዋና አላማው በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የዘርፉ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ አገልግሎችን ለማሻሻልና የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያግዝ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት መሆኑን የምክትል ከንቲባና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጃው ባይጨክን ባቀረቡት ሰነድ ገልፀዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤው ከኢንዱስትሪያሊስቱ፣ ከዘርፍ ማህበራት፣ ከኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና ከባለድርሻ አካላት የተውጣጡ 50 አባላት የያዘ ሲሆን ከአባላቱም ሰባት የስራ አስፈፃሚ አባለትን በመምረጥ ጉባኤውን ማጽደቁን ቢሮው ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ አስታውቋል