AMN – መስከረም 8/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያዊያን ፅናትና አሸናፊነት የተገለጠበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በቀጠናውና በአፍሪካ አህጉር ያላትን ሚና የሚያልቅ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰሞነኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል

በአዲሱ ዓመት አጥቢያ በይፋ ተመርቆ ስራ የጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ የዓለምን ትኩረት ስቦ የሰነበተ አጀንዳ መሆኑን የገለፁት ቃል አቀባዩ የበርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን አውታሮች የፊት ገፅ መነጋገሪያ ሆኗልም ብለዋል።
ኢትዮጵያን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በአሉታ ዘገባ ሲያሰራጩ የነበሩ የመገናኛ ብዙሀን ሳይቀር የግድቡን አዎንታዊ አበርክቶ ሲያስተጋቡ ሰንብተዋልም ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት።
የኢትዮጵያዊያን ኩራትና አንድነት ስበት የሆነው የህዳሴ ግድቡ የይቻላል መንፈስ ከቃል ተሻግሮ በተግባር የተገለጠበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያን የህልውና ጥያቄ የመለሰ ለአፍሪካዊያንም ዳግም መነቃቃትን የፈጠረ ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት፤ የኢትዮጵያን ቀጣናዊና አህጉራዊ ሚናን በእጅጉ የሚያልቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአቡ ቻሌ