በህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየውን የህዝብ ድጋፍ በሌሎች ልማቶች ለመድገም በቅንጅት ይሰራል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ

You are currently viewing በህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየውን የህዝብ ድጋፍ በሌሎች ልማቶች ለመድገም በቅንጅት ይሰራል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ

AMN – መስከረም 8/2018 ዓ.ም

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየውን የህዝብ ድጋፍ በሌሎች ልማቶች ለመድገም በቅንጅት እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ”በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ የደስታ መግለጫ ህዝባዊ ሰልፍ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ ግድቡ ጠንካራ ህዝብ መሆናችንን ለዓለም ያሳየ የጀግንነትና የህብረታችን ማህተም ነው ብለዋል።

”ይህንን ታሪክ ሰሪነታችንን አጠናክረን በማስቀጠል የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በህብረት መቆም አለብን” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ ህዝብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

በህዳሴ ግድብ የታየውን የህዝብ ድጋፍ በሌሎች የልማት ስራዎች በመድገም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

”ግድቡ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምዕራፍ ጅማሮ ነው” ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።

ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን የታየበት እና የአይበገሬነት ማረጋገጫ የሆነውን ግድብ በመገንባት ያሳየነውን ቁርጠኝነት ድህነትን ለማስወገድ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የክልሉ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review