የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ልዩ ስሙ ሚኪሊላንድ ኮንዶሚንየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተከሰተውን የመሬት መሰንጠቅ ተከትሎ የተከሰተዉ አደጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ ሳይንስ ባለሙያዎች ቡድን ጥናት አስጠንቷል፡፡
የጥናት ቡድኑም የደረሰበትን የጥናት ውጤት በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲቲዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ነገሰ ሞላ በአካባቢው የደረሰው የመሬት መሰንጠቅ መንስኤ ኮንዶሚኒየሞቹ ሲገነቡ የተቆፈረ ምልስ አፈር በአካባቢው መኖሩና፣ የኮንስትራክሽን ተረፈ ምርቶችም የተደፉበት ስፍራ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

እንደ ተመራማሪው ገለፃ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን ከአደጋው ለመከላከል የሚያስችሉ ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ ሀሳቦችም በጥናቱ ተመላክተዋል፡፡
የመሬት መሰንጠቅ ከደረሰበት በቅርብ እርቀት የሚኖሩ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ማዛዎር ጊዚያዊ መፍትሄ መሆኑን የጠቆሙት ከፍተኛ ተመራማሪው፣ የአካባቢውን የፍሳሽ አወጋገድ በአግባቡ ማስተካል ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ እንደሆነ በጥናቱ መረጋገጡና ተናግረዋል፡፡
አሁን የተከሰተው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ የበለጠ እንዳይስፋፋ አካባቢውን ከተሸከርካሪም ሆነ ከሰዎች እንቅስቃሴ መገደብ ተገቢ መሆኑንም ከፍተኛ ተመራማሪው ነገሰ ሞላ አሳስበዋል፡፡
በአስማረ መኮንን