ባርሴሎና በራሽፎርድ ግቦች ሲያሸንፍ፥ ሃለንድ ክብረ ወሰን አሻሽሏል

You are currently viewing ባርሴሎና በራሽፎርድ ግቦች ሲያሸንፍ፥ ሃለንድ ክብረ ወሰን አሻሽሏል

AMN መስከረም 09/2018

ኧርሊንግ ሃላንድ ታሪክ በሰራበት ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ናፖሊን አሸነፈ ፣ ባርሰሎናም በማርከስ ራሽፎርድ ግቦች ኒውካስትልን ረቷል።

ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ስታዲየም ናፖሊን አስተናግዶ 2ለ0 አሸንፏል። ግቦቹን ኧርሊንግ ሃላንድ እና ጀርሚ ዶኩ አስቆጥረዋል። ሃላንድ በቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን ግቦች 50 አድርሷል።

ኖርዌያዊ አጥቂ 50 ግቦችን በስሙ ያስመዘገበው በ49 ጨዋታዎች ብቻ ነው። በትንሽ ጨዋታ እዚህ የግብ መጠን ላይ የደረሰ ቀዳሚው ተጫዋች ሆኗል። ከዚህ ቀደም ሩድ ቫንስተርሎይ በ62 ጨዋታዎች 50 ግብ በማስቆጠር ባለ ክብረወሰን ነበር።

በጨዋታው ኬቨን ደብሩየና 10 ዓመት የተጫወተበትን ክለብ በተቃራኒ ገጥሟል። የ33 ዓመቱ ቤልጄማዊ የሜዳ ላይ ቆይታው 26 ደቂቃ ብቻ የፈጀ ሆኗል። የናፖሊ አምበል ጂኦቫኒ ዲ ሎሬንዞ በቀይ ካርድ መውጣቱ ተከትሎ አንቶኒዮ ኮንቴ ሌላ ተከላካይ ለማስገባት ደብሩየናን ቀይሮ አስወጥቷል።

በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ወደ ሴንት ጀምስ ፓርክ ያቀናው ባርሴሎና በማርከስ ራሽፎርድ ሁለት ግቦች ኒውካስትል ዩናይትድን 2ለ1 ረቷል። ከማንችስተር ዩናይትድ በውሰት ባርሰሎናን የተቀላቀለው ራሽፎርድ ለስፔኑ ክለብ ግብ ሲያስቆጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የኒውካስትልን ብቸኛ ግብ አንቶኒ ጎርደን ከመረብ አሳርፏል። ፍራንክፈርት ጋላታሳራይን 5ለ1 እንዲሁም ስፖርቲንግ ሊዝበን ኪራት አልማቲ 4ለ1 አሸንፈዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review