“ታሞ ከመማቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ የትኛውንም በሽታ ቀድሞ በመከላከል ጊዜን፣ ጉልበትንና የህክምና ወጭን ከመቆጠብ ባሻገር፣ መተኪያ የሌለውን የሰው ልጅ ህይወት ይታደጋል ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ቅድመ መከላከል አማራጭ የሌለው መንገድ ሆኖ የተቀመጠ አሰራር ቢሆንም፣ ማህበረሰቡ በዘልማድ ከህመም ስሜት በኋላ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የተለመደ ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአንጎልና ህብረ-ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሀናኒያ ጁንባይ፣ የዲስክ መንሸራተትን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።
የአንገት ዲስክ መሸራተትን ለመከላከል አንገትን ደፍቶ ለረጅም ሰዓት ስራ ላይ አለመቆየት፣ ትራስና ምኝታን ማስተካከል እና ቀላል እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ይመክራሉ።
የአንገት ዲስክ አከርካሪ አጥንት (ቨርተብሬ) ወደ ህብረ-ሰረሰር በአጥንት ተሸፍኖ ወደ ታችኛው የአካል ክፍል እንደሚሄድ ገልፀው፣ በአጥንቶች መካከል ያለው ጀል መሰል ፈሳሽን ተጠቅመን መገጣጠሚያችንን ለማንቀሳቀስ ስንቸገርና ህመም ሲሰማን የዲስክ መንሸራተት እንለዋለን ብለዋል።

ከቅድመ ጥንቃቄ መጓደል በተጨማሪ በድካም፣ በእርጅና፣ በአደጋ ጊዜ የመሰንጠቅ አደጋ ሲያጋጥም የዲስክ መንሸራተት የነርቭ እንቅስቃሴን ሊያውክ ይችላል፤ ይህም ዋናውን ህብረ-ሰረሰር ይጫናል ሲሉ ዶክተር ሀናኒያ አክለዋል።
የአንገት ዲስክ መንሸራተት የእጅ መደንዘዝ ፣ መስነፍና መዛል የሚያስከትል ሲሆን፣ ምልክቱም መንቀጥቀጥ፣ ንዝረትና ማቃጠል በዲስክ መንሸራተት የነርቭ መነካት ምክንያት የሚከሰት ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር ሀናኒያ የህክምና ዘዴውን ሲያብራሩም፣ በራሱ ጊዜ በ3 እና በ4 ሳምንታት የሚጠፋ እንዲሁም በቀላል የአንገት ፊዚዮ ቴራፒ ስፖርት፣ በመድኃኒትና በቀዶ ጥገና የሚጠፋ መሆኑን አስረድተዋል።
በአለኸኝ አዘነ