መሬት በሰዓት 1,600 ኪሎ ሜትር በምድር ወገብ ላይ በአስደናቂ ፍጥነት ትሽከረከራለች።
ይህ ሽክርክሪት በድንገት ለሰከንድ እንኳን ቢቆም ወይም ቢቋረጥ እጅግ አስከፊ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ። ድንገተኛ መቋረጡ የሚለቀው ከፍተኛ ሀይል ለከፍተኛ ውድመት እና ለረጅም ጊዜ አካባቢያዊ ለውጥ መንስኤ ሊሆን ይችላል።
ሽክርክሪቱ በተቋረጠበት ቅፅበት መሬት ጋር ያልተጣበቁ ቁስ አካላት ፣ እንስሳት እና የሰው ልጆች መሬት በምትሽከረከርበት ፍጥነት እኩል መንቀሳቀስ ይጀምራሉ፤ ይህም ከፍተኛ የህይወት መጥፋትን የሚያስከትል ነው። ህንጻዎች ይፈራረርሳሉ ፣ ከዚህ በለፈም የተለያዩ ቁሶች ከሽክርክሪቱ መቆም ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ከፍተኛ ሀይል ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ይገፋሉ።
የውሀ አካላት ቦታ መቀየር
በምድር ወገብ አቅራቢያ የሚገኙ ውቅያኖሶች በሽክርክሪቱ መቆም የተነሳ ወደ ሰሜን ፖል እንዲፈሱ እና የነበሩበትን ቦታ እንዲለቁ ሊያስገድዳቸው ይችላል። ይህም ቀደም ሲል በውሃ ተውጠው የነበሩ መሬቶች እንዲጋለጡ ፣ አዳዲስ የባህር ዳርቻዎች እንዲፈጠሩ እና ነባሮቹ በአስደናቂ ሁኔታ እንዲጠፉ ያደርጋል።
የቀን አቆጣጠር እና የአየር ሁኔታ መቃወስ
መሬት በተገቢው ኡደት መሽከርከሯን በምታቆምበት ጊዜ የቀን እና ማታ ልውውጥ ይቋረጣል። ይህም ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን የሚያስከትል ነው። በዚህ የተነሳም በአንድኛው የመሬት ክፍል ለበርካታ ጊዜ ቋሚ ጸሀይ ሲያገኝ ሌላኛው የመሬት ክፍል ደግሞ በቋሚነት ጨለማን ያስተናግዳል። ቀጥሎም በምድር ላይ ያሉ በህይወት የሚኖሩ ፍጡራን ለኑሮ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኙ በማድረግ የስነ-ምህዳር መዛባትን ያስከትላል።
የምድር ለውጦች
እሳተ ጎመራ ፣ የመሬት መንሸራተት ፣ መንቀጥቀጥ እና መሰንጠቅን የመሳሰሉ የምድርን መልኮች የሚቀይሩ ሁነቶች በፍጥነት እና በብዛት ያጋጥማሉ።
የማግኔቲክ ፊልድ እና የጨረራ ተጋላጭነት
የመሬት መሸከርከር በዳይናሞ ኢፌክት አማካኘነት የራሱን ማግኔቲክ ፊልድ ሀይል ያመነጫል፤ ምድር መሽከርከሯን በምታቆምበት ጊዜም ይህ ማግኔቲክ ፊልድ ከስራ ውጭ ስለሚሆን ፤ ሁሉም በህይወት ያሉ አካላት ለጎጂ የፀሐይ እና የጠፈር ጨረሮች እንዲጋለጡ ምክንያት እንደሚሆን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ላይ የወጣው የሳይንስ ዘገባ አመላክቷል።
በዳዊት በሪሁን