አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሚያጋጥማቸው ችግር ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልፀዋል፡፡
በአምባሳደር ግርማ ብሩ የተመራ የብሄራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የመስክ ምልከታ እያደረገ ይገኛል።
በመስክ ምልከታው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የካውንስሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የካውንስሉ አባል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የመስክ ምልከታው ዋና ዓላማ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ መቃኘትና እያጋጠሙ ለሚገኙ ችግሮች በቅንጅት መፍትሔ ለመስጠት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብዓትና በአሰራር ስርዓቶች ለሚያጋጥማቸው ችግር ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ አባላት የመስክ ምልከታቸውን በቦሌ ለሚና በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች መጀመራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉብኝታቸውም ስለ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ስላሉ እድሎች፣ እያጋጠሙ ስለሚገኙ ተግዳሮቶችና እየተወሰዱ ስላሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የቦሌ ለሚና የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች ባደረጉት ገለጻ ባለሀብቶች በራሳቸው ዲዛይን የመሥሪያ ቦታ እንዲገነቡና በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢኮኖሚ ዞኖቹ የምርት ስብጥርን ማሳደግ የሚያስችሉ የማስፋፊያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና ባለሀብቶች ወደ ምርት እንዲገቡ አስፈላጊው መሰረተ ልማት መሟላቱንም ነው ያብራሩት።
የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ የሥራ ኃላፊዎች ከውሃ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ከወሰን ማስከበር ጋር እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።
ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉ በተለያዩ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ምልከታውን እንደሚቀጥል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጿል።