የህብረት ስራ ማህበራት ለገበያ መረጋጋት ያላቸው አስተዋፅኦ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ የማሻሻያ ስራ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ የማህበራቱን የገበያ ድርሻ ለማሳደግና በማህበራቱ የሚታዩ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
ለኀብረት ሥራ ማህበራት ምቹ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲፈጠር ከመንግሥት፣ ከልማት አጋሮች እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በፋይናንስ ማስተሳሰር የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አንዱ የውይይቱ አካል መሆኑንም የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጌትነት ታደሰ ተናግረዋል።
ማህበራቱ የገበያ መረጃ ስርዓትን ከማሻሻል፣ ከውጪና ከአገር ውስጥ ገዢዎች ጋር ጠንካራ የገበያ ትስስር ከመፍጠር እና የምርት ብራንዲንግና የእውቅና ማረጋገጫ ከማግኘት አንጻር ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ በመወያየት አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ኮሚሽነሩ አክለዋል።
በአይናለም አባይነህ