በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል መሆኗን በግልጽ ማሳየት ችላለች

You are currently viewing በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል መሆኗን በግልጽ ማሳየት ችላለች

AMN መስከረም 9/2018

በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ አህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሔ አካል መሆኗን በግልጽ ማሳየት መቻሏን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ያካሄደው ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፈፃፀምና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ጉባኤው አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሄ አካል መሆኗን ያሳየችበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን ማስገንዘብ መቻሉንም አመላክተዋል።

ለአፍሪካ የተሰጠውን ያልተገባ ትርክት በመቀየር እየወሰደቻቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ማሳወቅ መቻሉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን የጋራ ድምጽ የያዘው የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን በማጽደቅ መጠናቀቁን አመላክተዋል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት “Africa Climate Innovation Compact” እና “African Climate Facility” የተሰኙ ኢኒሼቲቮች ይፋ መደረጋቸውን አንስተዋል።

በጉባኤው ከ25ሺህ በላይ ልዑካን መሳተፋቸውንና በርካታ የጎንዮሽ ሁነቶች መካሄዳቸውን ገልጸው፤ ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ማዕድናት እና የንጹህ ኢነርጂ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስትራቴጂዎችን ማጠናከር ሌላኛው ጉባኤው ከስምምነት ላይ የደረሰበት አጀንዳዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመሪዎች ደረጃም የአየር ንብረት ተጽእኖን መፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጽእኖን መቀነስ ላይ የመሪነት ሚናዋን ለአለም ማሳየቷን ገልጸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር የአዲስ አበባው ድንጋጌ ላይ ለአፍሪካ በሞዴልነት መጠቀሱን ማንሳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄዱን አስታውሰዋል።

ይህም በመልካም ሁኔታ መካሄዱንና በዚህም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሾች ላይ ተሞክሮዋን በስፋት ማካፈሏን ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review