በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ 123 ተጠሪጣሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ ተደረገ።
ህጋዊና መደበኛ የባንክ ስርዓትን ወደጎን በመተው በህገ-ወጥ እና ትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ እና ሌሎች ላይ ደግሞ የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በቅርቡ መግለፁ ይታወሳል።
በዚህም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለኤኤምኤን በላከው መግለጫ መሠረት በተለያየ ደረጀ በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሰማሩ የ123 ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ በዛሬው ዕለት ታግዶ የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በሂደት ላይ ይገኛል።
አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በርካታ ሰው የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን በህጋዊ መንገድ እያካሄደ በመሆኑ በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑም ተገልጿል።
ነገር ግን አንዳንድ አካላት አሁንም ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ለማትረፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን በክትትል መረጃዎች መረጋገጡም ተገልጿል።
በተጨማሪም አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑ የክትትል መረጃው ውጤት የሚያመላክት በመሆኑ ተጨማሪ ምርመራ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ይህ የወንጀል ድርጊት አንዱና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል።
ስለሆነም የህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ተግባር እና ሌሎች መሰል ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሠረት የወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳታፊ በሆኑት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አገልግሎቱ በልዩ ትኩረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።