በማረሚያ ቤቱ የትምህርት እድል ካገኙት መካከል አንዱ ነው። ይህንን እድል ማባከን ስላልፈለገ ውሎውን ከመፅሐፍ ጋር ማድረግ ምርጫው አድርጓል። ይህንን ማድረጉ ግዜውን ጠብቆ ለውጤት እንዲበቃ ምክንያት ሆኖታል።
አዲስ ሚድያ ኔትወርክም ከፍተኛ የውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በየቦታው እያሰሰ ውጤታቸው ምን ይመስላል? ውጤቱን ለማምጣት የተጠቀሙት ዘዴ ሌሎችን ያስተምር ዘንድ ተሞክሯቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት መካከል አባ ሳሙኤል ከፍተኛ የፌደራል የህግ ማረሚያ ተቋም ከሚገኙ ታራሚዎች ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ታራሚ ኤፍሬም አለማየሁ እና ታራሚ ያሬድ ስንታየሁ ጋር ኤ ኤም ኤን ቆይታ አድርጓል።
ታራሚ ኤፍሬም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል። ይህንን ውጤት እንዲያመጣ የመምህራን እገዛ እንዳለ ሆኖ የራሱም ጥረት ከፍተኛ እንደነበር ያስረዳል።
ለዓላማ ትኩረት መስጠት ለውጤት እንደሚያበቃ የገለፀው ታራሚ ኤፍሬም በየትኛውም ሁኔታ ሰው ውጤት ማምጣት ከፈለገ ቦታ እና ሁኔታ ምክንያት እንደማይሆን ማሳያ መሆናቸውን ይገልፃል።
ፈተናው ከመድረሱ ቀደም ብሎ መዘጋጀቱን ያስረዳው ታራሚው፣ በተለይም ከዚህ ቀደም ለፈተና የቀረቡ ጥያቄዎችን በድጋሚ ማየቱ ለውጤት እንዳበቃው ተናግሯል።
ታራሚ ኤፍሬም 427/600 በማምጣት የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ማምጣት ችሏል ። በትምህርት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ መሆን ከሚፈልጉት ነገር እንደማያግዳቸው ነው ታራሚው የተናገረው።
የጓደኛውን ሀሳብ የሚጋራው ታራሚ ያሬድ ስንታየሁ ደግሞ በማረሚያው ቤቱ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት መካከል ሌላኛው ነው ። ለዚህ ውጤት ያበቃው ፈተናው ከመድረሱ ቀደም ብሎ ዝግጅት ማድረጉን እና ከተማሪዎች ጋር በመረዳዳት መሆኑን ጠቁሟል።
ይህንን በማድረጉም 350/600 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ነው የገለፀው። የግዜ አጠቃቀሙ ለዚህ ውጤት መብቃቱ ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልፆ ያሉትን ትርፍ ግዜዎች በጥናት በማሳለፍ ለዚህ በቅቻለሁ ብሏል።
ጊዜ እና ሁኔታዎች ሳይበግረን ለዓላማችን ጠንክረናል ያሉት ታራሚዎቹ ይህንን በማድረጋችን ለውጤት በቅተናል ብለዋል። ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በስነ- ምግባር ከመቅረፅ ከስህተታቸው እንዲታረሙ ከማድረግ በተጨማሪ በትምህርት የተለያዩ ሙያ በማሰልጠን ብቁ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ሚናቸው ላቅ ያለ ነው።
የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ባለፈው ሳምንት ይፋ መድረጉ ይታወቃል ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ የ2017 የትምህርት ዘመን ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል 8.4 በመቶ ያህሉ ማለፋቸውን የትምህርት ሚንስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
በሔለን ተስፋዬ