የአለምን 15 በመቶ ህዝብ የሚያጠቃው ኩላሊት ጠጠር መንስዔ፣ ምልክት እና መከላከያ መንገዶች

You are currently viewing የአለምን 15 በመቶ ህዝብ የሚያጠቃው ኩላሊት ጠጠር መንስዔ፣ ምልክት እና መከላከያ መንገዶች

‎AMN- መስከረም 10 /2018 ዓ.ም‎

👉 የኩላሊት ጠጠር ምንድን ነው?

የኩላሊት ጠጠር በኩላሊት ውስጥ የጠጣር ነገሮች መጋገር ወይም መሰብሰብ ሲሆን፣ የጠጣር ነገሮቹም ምንጭ በሽንት ውስጥ የሚገኙ የምግብ ንጥረ ነገሮች ናቸው::

የኩላሊት ጠጠሮች በተለያየ መልኩ ሊከፈሉ ይችላሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ በሚገኙበት ቦታ ማለትም በሽንት ትቦና በሽንት ፊኛ፣ በጠጠሮቹ ውስጥ በሚገኙ ማእድናት ካልሺየም፣ ማግኒዢየምና አሞኒየም ፎስፌት፣ የሽንት አሲድ ወይም ሌላ ማእድናትን የያዙ ሊሆን እንደሚችሉ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል ።

ከ30-40 ባለው እድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ላይ በብዛት የሚከሰተው በሽታው በሴቶች ላይ ዘግይቶ ሊከሰት ይችላል።

ከ4 አይነት በላይ የኩላሊት ጠጠሮች የተለዩ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ምንም የህመም ስሜትና ጉዳት ሳያስከትሉ በሽንት መስመር ውስጥ አልፈው ከሰውነት ይወገዳሉ::

ነገር ግን የጠጠሮቹ መጠን ጨምሮ ከ3 ሚ.ሜ አካባቢ ከደረሱ፣ የሽንት ትቦን ሊዘጉ ይችላሉ::

👉 የኩላሊት ጠጠር መንስኤዎች

ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ የአመጋገብ ልማድ፣ በቂ ውኃ አለመጠጣት፣ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሥጋ (ፕሮቲን) መመገብ፣ ጨው የበዛበት ምግብ መጠቀም፣ የስኳር ምርቶች፣ ቸኮሌት፣ ኦቾሎኒ እና ለስላሳ መጠጦች ተጠቃሽ ናቸው።

👉 የህመሙ ምልክቶች

አብዛኛውን ጊዜ የኩላሊት ጠጠሮች በኩላሊት ውስጥ ካልተዘዋወሩ አሊያም ወደ ዩሬተር (ሽንትን ከኩላሊት ወደ ፊኛ የሚወስደው ቱቦ) ካልወረዱ ምንም አይነት የህመም ምልክት አያሳዩም።

ከዚህ ባለፈ፡-

• ጎንና ጀርባ ላይ ከፍተኛ ህመም መኖር

• ወደ ታችኛው የሆድ ክፍልና ብሽሽት አካባቢ የሚፈጠር ህመም

• ሽንት ሲሸኑ ህመም መኖር

• ቀይ ወይም ቡናማ የመሰለ የሽንት መልክ መከሰት

• ጉም የመሰለ ወይም ሽታ ያለው ሽንት

• ማቅለሽለሽና ማስታወክ

• ከተለመደው ጊዜ በላይ ሽንት መሽናት እና ሌሎችም ምልክቶች እንዳሉት የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል ።

👉 ወደ ህክምና ተቋም መሄድ የሚገባው መቼ ነው?

የሚከተሉት የህመም ምልክቶች ካሉ የህክምና ባለሙያዎችን ባስቸኳይ ማማከር ያስፈልጋል ።

• ህመሙ በጣም ከፍተኛ ከሆነና መቀመጥ ያለመቻል ወይም ምቾት የሚሳ ከሆነ

• ህመሙን ተከትሎ ማቅለሽለሽና ትውከት ከመጣ

• ከህመሙ ጋር ትኩሳትና ብርድ ብርድ ማለት ካለ

• ከሽንትዎ ጋር ደም የሚወጣ ከሆነ

• ሽንትን መሽናት መቸገር ሲፈጠር

• ከዚህ በፊት በቤተሰብ ወይም በራስ ላይ መሰል ችግር ከነበረ እና ሌሎችም

👉 በሸታውን የመከላከያ መንገዶች

የኩላሊት ጠጠር በሽታን በሁለት አይነት መንገድ መከላከል ይቻላል።

የመጀመሪያው የአመጋገብ እና የህይወት ዘይቤን በመቀየር ሲሆን ሌላው ደግሞ በህክምና እገዛ በማግኘት መከላከል ናቸው።

1. ውሃ አብዝቶ መጠጣት

ከ 12-14 ብርጭቆ ወይም ከ3 ሊትር በላይ ውሃ መጠጣት

ከምግብ በኋላ እና ከመኝታ በፊት 2 ብርጭቆውሃ ከእንቅልፍ ሲነሱ ደግሞ 1 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ልምድ ማድረግ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴና አድካሚ ስራ የሚሰሩ ከሆነ በላብ የሚወገደውን ውሃ ፈሳሽ በመውሰድ መተካት ተገቢ ነው።

በተጨማሪም ሞቃታማና ደረቅ የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ ሽንት በበቂ መጠን እንዲመረት/ እንዲወጣ ፈሳሽ በበቂ መጠን መጠጣት ይመከራል።

የሩዝ ውሃ እና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በብዛት መውሰድ ለመከላከል ጥሩ መንገድ ነው።

2. ከጨው መቆጠብ

ጨው በሽንት የሚወገደውን የካልሲየም መጠን የመጨመር ተግባር አለው፣ ስለዚህም በቀን ውስጥ ከ 6 ግራም የበለጠ ጨው መጠቀም አይመከርም

4. የተመጣጠነ ምግብ

እንደ ሙዝ፣ አናናስ እና ብርቱካን ያሉ ፍራፍሬዎችን፤ እንደ ገብስ እና አጃ የመሳሰሉ ጥራጥሬዎችን መመገብ ።

ማታ ከመኝታ በፊት ከበድ ያሉ ምግቦችን አለመመገብ እና ውፍረት መቀነስ ሌሎች መንገዶች ናቸው ።

👉 የህክምና መከላከያዎች

ጠጠር የሚታከምበት መንገድ እንደቦታው፣ መጠኑ፣ ምልክቶቹና የተሰራበት ውሁድ ይለያያል።

በአጠቃላይ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉ

እነዚህም፡-

ቀዶ ጥገና ሳንጠቀም የምናደረገው ህክምና እና በቀዶ ጥገና ናቸው።

1. ቀዶ ጥገና የማያስፈልገው መቼ ነው?

ከ 5 ሚ.ሜ በታች የሆኑ ጠጠሮች ምልክታቸው ከጀመረ ከ 3-6 ሳምንታት በራሳቸው በሽንት ይወገዳሉ። በዚህ ጊዜ ሀኪሙ በዋነኝነት ምልክቶቹ እና ጠጠሮቹ ከታካሚው ያለ ቀዶ ጥገና እንዲወገዱ ማድረግ ይሆናል።

አጣዳፊ ህመም ያለዉ ታካሚ በጡንቻ ወይም በደም ስር የሚሰጥ ማስታገሻ (NSAIDs) ሊያስፈልጉት ይችላል።

ቀላል ህመም ከሆነ የሚዋጡ ማስታገሻዎች በቂ ናቸው።

2. በቀዶ ጥገና የሚወገድ ጠጠር

ቀዶ ጥገና በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው በራሳቸው ያልተወገዱ ጠጠሮችን፣ ከ 6 ሚ.ሜ በላይ የሆኑ ጠጠሮችን፣ የሽንት ፍሰትን የሚዘጉ ጠጠሮችን እና በተደጋጋሚ ኢንፌክሽን የሚፈጥሩ ጠጠሮችን ለማስወገድ ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት የዓለምን 15 በመቶ ህዝብ የሚያጠቃው ኩላሊት ጠጠር በጊዜ ካልተደረሰበት የኩላሊት መዳከም እና አለፍ ሲልም ሞትን ጨምሮ ለከፋ ጉዳት ሊያጋልጥ ይችላል ።

ስለሆነም የህይወት ዘይቤ እና አመጋገብን ከማሻሻል ባለፈ፣ የበሽታው ምልክቶችን በትኩረት መከታተል እንደሚገባ ከአለም ጤና ድርጅት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review