የመደመር መንግሥት

You are currently viewing የመደመር መንግሥት

”ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ ይመርጣል”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባን ለመለወጥ የተጀመረው ስራ አዲስ የስራ ባህልን ያለማመደ እንደሆነም በተምሳሌትነት ቀርቧል

ኢትዮጵያ በረዥም የታሪክ ጉዞዎቿ ውስጥ ቀላል የማይባሉ ምዕራፎችን በብዙ ስቃይ ውስጥ አሳልፋለች፡፡ ለህመሟ ፈውስ ይሆን ዘንድ የምትወስዳቸው መድሐኒቶች የተለመዱና ሁሉንም ህመም የማይፈውሱ እንደሆኑ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሙሐመድ በሽር እንደሚሉት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ እስከ አሁን ሀገራችን የተከተለችው መንገድ  በአመዛኙ ተመሳሳይና የሀገሪቱን ችግር በዘላቂነት ያልፈታ ነው፡፡ በመሆኑም አዋጭና ከሀገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች የሚነሳ መፍትሔን ይዞ መቅረብ ምን ያህል አዋጭ መሆኑን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየን ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ረቡዕ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጻፉት “የመደመር መንግሥት’’ የተሰኘ 4ኛው መፅሐፍ ዋና ጭብጥና የተመላከቱ እውነተኛ አስረጂዎች ምስክር ናቸው ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው፣ በመፅሐፋቸው ምረቃ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክትም የመደመር መንግሥት ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ ይመርጣል ማለታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዕለቱ ባደረጉት ንግግርም “የመደመር መንግሥት” የተሰኘው መጽሐፍ ታሪክ ሰሪዎች እንጂ ታሪክ ዘካሪ አንሆንም በሚል መልዕክት የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፣ “የመደመር መንግሥት” ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ ይመርጣል ብለው፣ ይህንን ጉዞ ለማሳየት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሱዳን በቂ አስተማሪ ምሳሌ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡

በዚህም፣ “እኛ ስንለወጥ ሱዳን ሰላማዊ ሀገር ነበረች፤ አሁን ግን የተዛባ ጥያቄ ሲነሳ ቀድሞ በልጆቿ የገነባችውን የካርቱም ኢንተርናሽናል ኤርፖርት አፍርሳዋለች፡፡ ሱዳኖች የተከተሉት እና የመረጡት መንገድ አፍራሽ በመሆኑ ለችግር ተዳርገዋል” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “እኛ ደግሞ በገንዘብም፣ በሀሳብም፣ በአሰራርም፣ የገዘፈውን ሕዳሴ ከነስብራቱ ተቀብለን ለፍጻሜ ማብቃት ችለናል” በማለት የመደመር መንግሥት ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ መምረጡንና ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑም በተጨባጭ ማስረጃዎች አብራርተዋል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሙሐመድ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ አዲስ ታሪክ ያስፈልገዋል። እስከ አሁን በሄድንበት መንገድ ሀገርን ቀና የሚያደርግ ምዕራፍ ላይ አልደረስንም። ይህም ከመሰረታዊና ሁሉንም አካታች ከሆነ ችግርና መፍትሔ ባለመነሳታችን ነው፡፡ በመሆኑም የመደመር መንግስት አዲስና የሀገርን መሰረታዊ ችግር በዘላቂነት የሚፈቱ አቅጣጫዎችን እየተከተለ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ታላላቅ የሚባሉ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው፣ እንደ ሀገር እንቅፋት የሆኑብንን ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን እና ብዙ ርቀት መጓዙን፣ የሀገር በቀል ኢኮኖሚው በለውጥ ምዕራፍ ላይ መሆኑን፣ በትምህርት፣ በጤናና መሰል ዘርፎች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን እንዲሁም የሀገርን ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊና መሰል ከፍታዎች ማረጋገጥ የሚያስቸለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መሰረት ያደረጉ  ጫናዎችን ተቋቁሞ ለፍፃሜ ማድረሱ በትክክልም የመደመር መንግስት ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ ይመርጣል መባሉን በተጨባጭ የሚመሰክሩ ናቸው ብለዋል፡፡

“የመደመር መንግሥት” የኢትዮጵያ ብልፅግና ምኞት ብቻ ሳይሆን እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መጽሐፉ የኋልዮሽ ጉዞውን ከዳሰሰ በኋላ መዳረሻውን በግልፅ የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል፡፡

“የመደመር መንግሥት” እቅዶች የማይፈፀሙ በመሻት ብቻ የሚቀሩ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በሚያረጋግጥ መልኩ በተያዘላቸው ጊዜ የሚፈፀሙ መሆናቸውንም በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ እንደ ሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በዓባይ ግድብ እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች የተመዘገበው ስኬት የመደመር መንግስትን የማቀድ እና የመፈፀም አቅም ለዓለም ያሳዩ መሆናቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም በራስ አቅም፣ በራስ ገንዘብ እና በአጠረ ጊዜ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ ምሳሌ እንደሚያደርጓትም ተናግረዋል፡፡ “የመደመር መንግሥት” ማጠንጠኛውም  “አራት መ” መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የመጀመሪያው “መ” መነሻ ነው ብለው፣ መነሻውም ቁጭት መሆኑን ነው ያስረዱት።

“ኢትዮጵያ ለምን ድሃ ሆነች? ኢትዮጵያ ለምን ተረጂ ሆነች? ኢትዮጵያ ከማን ስለምታንስ ነው የምትረዳው? የሚሉ የቁጭት ጥያቄዎች እና ምክንያት ፍለጋ ነው መነሻው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አሳማኝ ምክንያት ካልተገኘለት ቁጭት ያንገበግባል፤ እንቅልፍ ይነሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ለመደመር መንግሥት መነሻ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ “የመደመር መንግሥት” ውጤት ከሰማነው፣ ካነበብነው ብቻ ሳይሆን በተግባር ስንሞክር ካየነው ውጣ ውረድ ጭምር የተቀዳ ነው” ሲሉ በመፅሐፋቸው ምረቃ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው እንደሚሉትም ሀገር በዘላቂነት ከፍ ልትል የምትችለው በተጨባጭ ቁጭት ተነስቶ፣ ከተግባራዊ እውነታዎች፣ ከችግር ፈች ብልሃቶች፣ ከትላንት ተምሮ፣ ዛሬን አይቶና ነገን ታሳቢ አድርጎ በቆራጥነት በሚሰራ መንግስትና ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም የመደመር መንግስት መፅሐፍ በዚህ ልክ የተዘጋጀና በተግባርም እየተገለጠ ያለ በመሆኑ በዚህ ልክ አቅጣጫን ግልፅ አድርጎ በተግባር እየመዘኑ መጓዙ እንደሀገር አስተማማኝ ከፍታ ላይ ለመድረስ ትልቅ ጉልበት እንደሚሆንም አብራርተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ከፖለቲካ ኢኮኖሚ አንጻር ያለውን ዕይታ በሚመለከት ዳሰሳ አቅርበዋል። በዚህም ፀሐፊው በመደመር መንግስት መፅሐፍ እንዴት ኋላ ቀረን? ከዓለም ጋር የት ላይ ተላለፍን? ብለው በቁጭት በመጠየቅ ችግሮችንና ስብራቶችን ለመሻገር ከውስጥ ወደ ውጭ ማየት አለብን ማለታቸውን ጠቁመዋል።

በመጽሐፉ ምረቃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የመጽሐፍ ዳሰሳ ካቀረቡት መካከል አንዱ ናቸው። በዚሁ ወቅት እንደገለፁት መጽሐፉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ ነው ብለው፣ በተለይ የኢትዮጵያን ችግሮች በጥልቅ የዳሰሰና ተግባራዊ መፍትሔዎችን ያመላከተ መጽሐፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም፣ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አስተሳሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ ከቁጭት የሚነሳ መጽሐፍ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ መጽሐፉ ነገሮችን አፍርሶ ከመስራት ይልቅ አዎንታዊውን ማስቀጠልና አሉታዊውን ማስተካከል ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት የሄደችበትን ተቸካይ የፖለቲካ አካሄድ የቀየረ አተያይ እንደሆነ አስታውሰው፣ ይህም ፖለቲካችንን ያሸነፈ አካል እንደፈለገ ሁሉን ይጠቅልል ከሚል አካሄድ የሚያወጣ  እንደሆነም መስክረዋል፡፡ “የመደመር መንግሥት” እኔ የፈለኩት ካልሆነ ከሚል የዜሮ ድምር ጨዋታ መውጣት የሚቻልበትን ዘመናዊ የፖለቲካ አካሄድ ያመላከተ መጽሐፍ እንደሆነም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የተከማቸ ችግር ለመፍታት የተተገበረው የመፍጠርና መፍጠን መፍትሔ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ እንደሆነም በተምሳሌትነት አቅርበዋል፡፡ አዲስ አበባን ለመለወጥ የተጀመረው ስራ አዲስ የስራ ባህልን ያለማመደ እንደሆነ የመሰከሩት አቶ ጌታቸው፣ በቀጣይ በአዲስ አበባ የታየው አዲስ ተስፋ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ እንዲሰፋ መረባረብ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ችግሮች ላይ ንደፈ ሃሳባዊ ትንተና ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽ የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለችግሮች አውዱን የተገነዘበ ሙሉ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚገባ በመጽሐፉ በግልጽ መቀመጡን ጠቅሰው፣ ይህም አንድ መንገድን ብቻ ከሚከተል የርዕዮት እስረኝነት የተላቀቀ አካሄድ ነው ብለዋል። መጽሐፉ የያዛቸው ትንተናዎችም በምክንያታዊነት ላይ ያረፉና ለምክንያታዊነት ክፍት ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላኛው በመጽሐፉ ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀረቡት የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ መጽሐፉ ትናንትን በልኩ የሚገነዘብና በትናንት እሳቤ ላይ ያልቆመ ስለመሆኑ ተናግረዋል። መፅሐፉ፣ የዛሬ ችግሮችን በተገቢው መንገድ እንደሚዳስስ ጠቅሰው፣ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች የተሻለ ነገን ከመገንባት የሚያስቆሙ እንዳልሆኑ በግልጽ እንደሚያመላክት አብራርተዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ ባነሷቸው ሀሳቦች እንደሚስማሙ የጠቆሙት ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሙሐመድ በሽር እንዳሉት፣ “የመደመር መንግሥት” ለአፍሪካ ጭምር የሚበጁ ሃሳቦችን ይዟል፡፡ ያልተሄደበትን መንገድ መጓዝ የሚመርጠው የመደመር መንግሥትም የሀገሪቱን ስብራቶች እየጠገነ፣ ህመሞቿን በዘላቂነት እየፈወሰ ከሀገር አልፎ እንደ አህጉርም ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ውጤቶችን እያስመዘገበ ስለመሆኑ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review