ግድቡ የፈነጠቀው የኢንዱስትሪዎች ተስፋ

You are currently viewing ግድቡ የፈነጠቀው የኢንዱስትሪዎች ተስፋ

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ መሆኑን የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ገልፀዋል

ኃይለገብርኤል ዋቅጅራ ይባላሉ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ለሀገራቸው ዘምተዋል። አሁን ላይ በ2000 ዓ.ም ኃይለገብርኤል፣ ፈረደና ጓደኞቻቸው የቤትና ቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ የሚል ድርጅት አቋቁመው በስራ አስኪያጅነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ትልቅ ርዕይን በመሰነቅ፤ በትንሽ ገንዘብ፣ የቤተሰብን ቦታ እና የተወሰነ ማሽን በማቀናጀት ሥራውን የጀመረው ይህ ድርጅት፤ አጀማመሩን እና ያለፈበትን መንገድ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለገብርኤል እንዲህ ያስታውሳሉ፤ “እኔ ማሽን አዋጣሁ፡፡ አንድ ጓደኛችን ሦስት ሺህ ብር አመጣ። አንዱ ደግሞ የቤተሰቦቹን ይዞታ ለመሥሪያ ቦታነት አስፈቀደ፡፡ ሌሎቹም የሚችሉትን አደረጉና ወደ ሥራ ገባን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የገባንበት ሥራ ከጅምሩ በችግሮች መፈተኑ አልቀረም፡፡ ለሥራው አዲስ ከመሆናችን በተጨማሪ፤ ለሥራ ማስኬጃ ይዘነው የነበረው ካፒታል ምንም ሊያደርግልን አልቻለም፡፡ በዚህም ድርጅቱን በጋራ ከመሰረትነው አስር አባላት መካከል አራቱ በመሃል ወጡ፡፡ እኛ የቀረነው ተስፋ ሳንቆርጥ፤ ችግሮችን እየፈታን፤ ያለንን እያሳደግን ለመቀጠል ወስነን ተንቀሳቀስን፡፡ ቢዘገይም ውጤት ማየት ቻልን፡፡”

ለሃያ ዓመት በተቃረበ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ድርጅት በተስፋ ሰጪ የስኬት ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ የምርቱ ዓይነትም ሆነ ተደራሽነቱ አድጓል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የቢሮ ዕቃዎችን ለማምረት እና ለማቅረብ የሚያስችለውን ከፍተኛ የማዕቀፍ ግዢ ጨረታ በማሸነፍ፤ ከመንግስት ጋር ውል ተዋውሎ ወደ ማምረት ገብቷል፡፡ ለ64 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 41 ሠራተኞች ቋሚ ናቸው፡፡

ድርጅቱ ከቤት እና ከቢሮ ዕቃዎች በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) መጠቅለያ ማሽን (ድራም) በማምረት ለተጠቃሚዎች ሲያደርስ ቆይቷል፤ እያደረሰም ይገኛል፡፡ ከውጭ ይገባ የነበረውን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የቻለውን ይህንን ማሽን ለመሥራት የተቻለበትን አጋጣሚ ለሥራው የአንበሳውን ድርሻ የተወጡት አቶ ኃይለገብርኤል ዋቅጅራ እንደሚከተለው ያስታውሳሉ፤ “የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) መጠቅለያ ማሽን (ድራም) የማምረት ሥራ የጀመርነው ቻይና ሄጄ የተመለከትኩትን ወደ ተግባር መለወጥ በመቻሌ ነው፡፡ በዚያ ካየኋቸው በርካታ የማምረቻ ዘርፎች እና የአመራረት ሂደቶች አንዱ ይኸው የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) መጠቅለያ ማሽን (ድራም) ማምረቻ ነበር፡፡ በጉብኝቴ ያየሁትን እና ከዩቲዩብ መረጃዎችን በማጣመር በራስ አቅም የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) መጠቅለያ ማሽን (ድራም) ለማምረት ከሥራ አጋሮቼ ጋር በመሆን ሞከርን፤ ተሳካልን፡፡”

የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) መጠቅለያ ማሽን (ድራም) ምርት ለዓመታት በብቸኝነት ሲያመርት የቆየው ይኸው ድርጅት፤ የምርቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ሥራ ላይ የተሠማሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶች  መሆናቸውን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ገልፀዋል፡፡  በብቸኝነት ይዞት የቆየውን ሥራ በሂደት ልምድና ተሞክሮውን ለሌሎች በማጋራት መሠል ማሽን በሀገር ውስጥ ድርጅቶች በስፋት እንዲመረት ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ፤ በቀጣይ ስላቀደው የማስፋፊያ እና የደረጃ ማሻሻል ዕቅድ እንዲሁም የሥራ እንቅስቃሴ ሂደት በማስመልከት አቶ ኃይለገብርኤል ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፤ በመቋቋም ላይ ያለውና የማስፋፊያው አንድ አካል የሆነው አዲሱ ድርጅት በዋናነት የመኪና አካላትን የሚያመርት ነው፡፡ ለድርጅቱ መቋቋም መነሻ ሃሳብ የተገኘው ከቻይና የሥራ ጉብኝት ተሞክሮ ነው፡፡ በቻይና ትላልቅ ማሽኖች ይመረታሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ከቀላል እስከ ከባድ ተሽከርካሪዎች በቻይና ተሠርተው ለዓለም ገበያ ይቀርባሉ። እነዚህ ተሽከርካሪዎች የመጨረሻ ምርት ሆነው የሚወጡት፤ ሁሉ ነገራቸው በአንድ ኢንዱስትሪ ተመርቶ አይደለም። እያንዳንዱ የተሽከርካሪው አካል ራሱን በቻለ የተለያየ ኢንዱስትሪ ነው የሚመረተው፡፡ ስለዚህ የኛ አዲሱ ድርጅት የተለያዩ የተሽከርካሪ አካላትን በማምረት፤ ተሽከርካሪ ለሚያመርቱ ወይም ለሚገጣጥሙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚያደርስ ይሆናል፡፡

ይህ በማስፋፊያው የተካተተው አዲስ ድርጅት በተጨማሪም፤ ሚስማር ማምረቻ፣ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን እና ሌሎች በሂደት የሚካተቱ የሥራ ዘርፎች በዕቅዱ ያካተተ ሲሆን፤ በ200 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚቋቋም ነው። ወደ ሥራ ሲገባ እስከ 200 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች በድርጅቱ ውስጥ የሚሠሩበትን ዕድል የመፍጠር ዓላማም አለው፡፡

ድርጅቱ ፕሮጀክቱን ሠርቶ ለመንግስት አቅርቧል፤ ተቀባይነትንም አግኝቷል፡፡ ማስፋፊያው የሚገነባበትን ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ ተረክበው፤ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለመቀበል በሂደት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ ይህ እንዳለቀ ወደ ግንባታ ለመግባት የተዘጋጁት የድርጅቱ መስራች አባላት፤ መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ለሚገኙ ድርጅቶች ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አንስተው፤ ይህን መሰል ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ያፈራቻቸው ታታሪ ሥራ ፈጣሪዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል፡- የሮሰን ጨርቃ ጨርቅ አምራች እና የህትመት ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ስለድርጅቱ አሁናዊ የሥራ እንቅስቃሴ እና በቀጣይ ለመፈፀም ስለተዘጋጀበት ዕቅዱ ላነሳነው ጥያቄ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅሬ ታፈሰ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻ፤ ድርጅቱ በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝና 354 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ የማምረቻ ሼድ ውስጥ ነው ሥራውን እያከናወነ ያለው፡፡ 74 ማሽነሪዎችን በመጠቀም፣ 56 ባለሙያዎችን በሥራ ላይ በማሰማራት በዋናነት የስፖርት ትጥቆችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ምርቶቹንም አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ያሰራጫል፡፡

አክለውም፤ “ድርጅታችንን ለማስፋፋት በእንቅስቃሴ ላይ ነን። የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጠን ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበን ጥሩ ምላሽ አግኝተናል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ከተገነቡ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሼዶች መካከል፤ ለእኛ የሥራ እንቅስቃሴ አመቺ የሆነውን ለመረከብ በሂደት ላይ ነን፡፡ በሌላ በኩል የመሥሪያ ማሽኖችን አዘን ከውጪ እስኪመጡ እየተጠባበቅን ነው። በማስፋፊያ ፕሮጀክታችን ውስጥ አዳዲስ የሥራ ዓይነቶችን እናስጀምራለን። አሁን ከምናመርተው የተሻለ ጥራትና ዲዛይን ያላቸውን የአልባሳት በተለይም የስፖርት ትጥቅ ምርቶችን የማምረት ዓላማ አለን፡፡ ሥራውንም በቀን 24 ሰዓት፣ በሳምንት 7 ቀናት ያለማቋረጥ ለማከናወን አቅደናል። የምናስገባቸው ማሽኖች በጣም ዘመናዊ የሚባሉ ናቸው። ከስፌት በተጨማሪ በተለያየ ዲዛይን የህትመት ሥራን የሚፈፅሙ ይሆናል” በማለት አብራርተዋል፡፡

ድርጅቱ ማስፋፊያ፤ የአልባሳት ዲዛይን፣ ህትመት፣ ስፌት እና ሽያጭን አቀናጅቶ የያዘ ነው፡፡ በማምረቻ ቦታው ላይም የራሱ ሱቅ ይኖረዋል፡፡ ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት አዳዲስ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ምርቱ በሂደትም ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የመግባት ዓላማን አስቀምጧል፡፡ ይህንን ለማሳካት በድርጅቱ የተፈጠረው የሥራ ባህል እና በመንግስት እየተደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ሥራ አስኪያጇ አልሸሸጉም፡፡

ኢንዱስትሪዎችና የሕዳሴ ግድብ የነበሩበትን የሥራ ዘርፍ በዓይነት፣ በመጠን፣ በጥራት እና በተወዳዳሪነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ከጫፍ የደረሱት ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ከፍተኛ ደስታ እና የሥራ መነቃቃት እንደፈጠረባቸው በሥራ አስኪያጆቻቸው አማካኝነት ገልፀዋል፡፡

መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖራቸው ሲያደርግ ቆይቷል” ያሉት አቶ ኃይለገብርኤል::

በውጭ ሀገራት ተመርተው የምናስገባቸውን የተለያዩ ማሽኖችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሀገር ውስጥ ምርት ሊተኩ የሚችሉ ሥራዎች በሼዶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ስፍራዎች ተዓምር በሚባል ደረጃ በብዛት እየተሠሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እነዚህ አስደናቂ የቴክኖሎጂ እና የማሽን አምራች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በፍጥነት እንዲያድጉ እገዛው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ትላልቆቹ ኢንዱስትሪዎችም ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ፍቅሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት ግድቡ  ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ለድርጅታችንም ሆነ ለሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡

ምርትን በብዛት እና በጥራት ለማምረት አቅም ይፈጥራል፡፡ በቀን ብቻ የተወሰነውን የሥራ እንቅስቃሴ፤ ሌሊትም በቋሚነት የመሥራትን ተነሳሽነት ይፈጥራል። ምርታማነትን ይጨምራል፤ ጥራትን ያሳድጋል፡፡ የሥራ ባህልን ያዳብራል፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ፣ እንደ ድርጅት ብሎም እንደ አገር ፈጣን ዕድገት እንዲመዘገብ ያግዛል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በይፋ መመረቅ ይዞት የሚመጣው ትሩፋት ሥራ አስኪያጇ ይህንን ብለዋል፤ “ለሥራ የምናስገባቸው አዳዲሶቹ ማሽኖች በሶፍትዌር ፕሮግራም ተደርገው፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቅመው፣ በአንድ ትዕዛዝ ያለማቋረጥ ለረጅም ሰዓታት በምርት ሂደት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ማሽኖቹ ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ ከመጠቀማቸው ባለፈ፤ በመሃል የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ቢከሰት የምርት ሂደታቸው ይስተጓጎላል፡፡ የተቋረጠው ኃይል ሲመጣ፤ የተስተጓጎለው የምርት ሂደት ከተቋረጠበት አይቀጥልም። እንደ አዲስ የሶፍትዌር ፕሮግራሙን መሙላት፣ ትዕዛዙን ማስተካከል እና ማስጀመርን ይጠይቃል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ በኃይል አቅርቦት ማደግ ላይ አይተኬ ሚና ስለሚጫወት  ለድርጅታችን የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡” 

ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አበባ ታመነ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ እንደሳቸው ምላሽ ከሆነ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ መብቃቱና መመረቁ፤ እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረ ነው፡፡ በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲያድግ፣ ጥራታቸው እንዲሻሻል፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸው እንዲጎለብት፣ የሥራ ባህላቸው እንዲዳብር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝነቱ የላቀ ነው። ምርታማነታቸው ሲያድግ፣ በጥራት እና በተወዳዳሪነታቸው ሲሻሻሉ የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ያስፋፋሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድልን ይፈጥራሉ፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ይተካሉ። ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ያስገኛሉ፡፡

የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚዋ አክለው እንደገለፁት፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ውጤታማነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪዎችን የሽግግር ሂደት በተሳካ ሁኔታ ማስኬድ ይገባል። ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ፣ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደግና ማሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባሉት መዋቅሮች አማካኝነት ሲሠራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡ በሀገሪቷ ያሉ ሁሉም ወረዳዎች ያላቸውን ፀጋና አቅም ታሳቢ ያደረገ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርፆ፣ ‘የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ንቅናቄ’ በሚል መርህ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ይህንንም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እየተገበሩት  ሲሆን፤ እያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ አንድ፣ ቢበዛ ሦስት ደረጃቸውን የጠበቁ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋምና ለውጤት የማብቃት ተልዕኮን ማሳካት ይጠበቅበታል፡፡

የ‘ኢንዱስትሪያላይዜሽን ንቅናቄ’ እንዲሳካ እንደ መንግስት መደረግ የሚገባቸው ድጋፍና ክትትሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ አበባ፤  ከእነዚህ ውስጥ፡- የመሥሪያ (የማምረቻ) መሬት፣ የፋይናንስ ብድር፣ የማሽን እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና ለአገልግሎት መብቃት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተነቃቃ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አቅም ይፈጥራል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ደረጃቸውን በማሳደግና በማሻሻል (ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ) ሽግግር እንዲያደርጉ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ 

እንደሀገር እየተተገበረ ካለው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር በማስተሳሰር ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሚና እንዲህ አብራርተዋል፤ “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከያዛቸው በርካታ ዓላማዎች መካከል፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግሮችና ማነቆዎች በመፍታት ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት እንዲያሳዩ ማስቻል የሚለው አንዱ ነው።  ኢንዱስትሪዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥ፡- ከመሥሪያ ቦታ፣ ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከማሽን፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ … ጋር የተያያዙት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥራዎችን በጋራና በቅንጅት ለመፈፀም ወሳኝ ባለድርሻ አካላት ካደረጋቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዱ ነው። የኢንዱስትሪዎች ሁነኛ መሣሪያ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል በበቂና ባልተቆራረጠ ሁኔታ እንዲደርሳቸው የማድረጉን ኃላፊነት የሚወጣው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁ ይህንን ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ ለመፈፀም ዕድል ይፈጥርለታል። ይህም እንደ ሀገር የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በፍጥነት ያሳድገዋል፤ ውጤታማም ያደርገዋል፡፡”

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review