የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የበለጠ እንዲደምቁ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ ተገልጿል
“ትንሿ ኢትዮጵያ” በሚል ብዙዎች የሚጠቀሙትን መጠሪያ በተግባር ገልጻ ማረጋገጥ ችላለች፤ አዲስ አበባ፡፡ ለዚህ ማዕረግ ያበቃትን በተግባር የተገለጠ ማስረጃ መዘርዘር ቀላል ነው። ሌላውን ትተን፤ በታላቅ ድምቀት የሚከበሩትን የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓላትን በአብነት ማንሳት ለአዲስ አበባ “የትንሿ ኢትዮጵያ” ማዕረግን የመቀዳጀት ሚስጥር እንረዳለን፡፡ እነዚህ ሁለት የአደባባይ በዓላት በቀናት ልዩነት ውስጥ የሚከበሩ ናቸው፡፡ የሚከበሩባቸው ሥፍራዎች (መስቀል አደባባይ እና የሆራ ፊንፊኔ) በቅርብ ርቀት ላይ መገኘታቸው በበዓላቱ ላይ ለሚታደሙ ትዝታን የሚፈጥር፣ የእርስ በእርስ መስተጋብርን የሚያጠናክር፣ አንድነትንና ህብረትን የሚያጎለብት ልዩ አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡
የአዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ ምስክሮች
“ስለአዲስ አበባ አስገራሚ ለውጥ ለመናገር ምስክር አያሻም፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ በየዕለቱ በፈጣን ዕድገት እየተጓዘች ነው፡፡ እድገትና ለውጧ እንኳን ከሌላ ቦታ ለመጣ ሠው ይቅርና፤ ለእኛ ለነዋሪዎቿም የሚያስደንቅ ነው” የሚሉት አቶ አሸናፊ ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኙት አቶ አሸናፊ ተወልደው ያደጉት፣ ትዳር ይዘው ልጆችን ያፈሩት በአዲስ አበባ ሲሆን፤ ለከተማዋ ልዩ ፍቅር እንዳላቸው ከቃላት በላይ ገጻቸው ላይ የሚንፀባረቀው ስሜት ይናገራል፡፡
አቶ አሸናፊ እንደሚሉት፤ ከተማዋ ለኑሮም፣ ተንቀሳቅሶ ለመሥራትም፣ ልጆችንና ቤተሰብን ይዞ ወጣ ለማለትም የምትመች አልነበረችም፡፡ ንፅህናቸውን ያልጠበቁ ጠባብ መንገዶች፣ ከአቅማቸው በላይ ነዋሪዎችን የያዙ የተጎሳቆሉ መንደሮች በብዛት ነበሩ፡፡ የአንዳንድ አካባቢዎች ችግር ከዚህም የከፋ ነበር። ክረምት ሲገባ ወይም የበጋው ሙቀት ሲያይል ወረርሽኞች ጭምር እስከመከሰት የሚደርስበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን በከተማዋ እየተከናወነ ባለው ልማት እነዚህ ችግሮች ተፈተዋል፡፡ ውበት፣ ፅዳት እና ምቹነት የከተማዋ መገለጫ ሆኗል፡፡ በቆሻሻ ተበክለውና ደፍርሰው የማያስጠጉ ወንዞች ሳይቀሩ፤ በሚያጓጓ ለውጥ ላይ ናቸው፡፡ ጎዳናዎቿ የሚያምሩ ውብ ከተማ ሆናለች፡፡ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለሚያከብራቸው የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት የበለጠ ድምቀት ይፈጥራል፡፡

ወይዘሮ ፅጌ ታምራት በበኩላቸው “ይህን መሰል ለውጥ ከእኛ ባሻገር ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን ትልቅ ሀብት እንደማስቀመጥ ነው። በተለይም የመስቀል፣ የኢሬቻ እና መሰል በአላትን በአደባባይ ወጥተን ስናከብር የከተማዋ ውበት የበለጠ ያምራል፡፡ ይህም ሠው በአደባባይ ወጥቶ የሚያከብራቸው በዓላት በናፍቆት እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል፡፡ እኔም ይህ ስሜት ነው ያለኝ” በማለትም ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
ሁሉም የሚመሰክርለትን የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ለውጥ በተመለከተ ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፅፈው ለንባብ ያበቁት “የመደመር መንግሥት” መፅሐፍ ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ያነሱትን ሃሳብ እዚህ ላይ እናስታውስ፡፡ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአዲስ አበባን ተጨባጭ ለውጥ በምሳሌነት ጠቅሰዋል። በተለይ በኮሪደር ልማት እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ የታየውና እየታየ ያለው አበረታች ለውጥ፤ ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
“በአዲስ አበባ ከተማ እየመጣ ያለው ለውጥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በመላው አፍሪካ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህንም ምክንያት፤ “በመዲናዋ የተከናወነው እና እየተከናወነ ያለው ሰፋፊ የልማት ሥራ በራስ አቅም፣ በራስ ገንዘብ፣ ባጠረ ጊዜ፣ ከመቆሸሽ፣ ከጨለማ ልምምድ የወጣ እና ለዜጎች መኖሪያነት የተመቸ ከተማ መገንባት እንደሚቻል በተግባር ያሳየንበት አንዱ ሥራ በመሆኑ ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማትን በተመለከተ በመድረኩ ላይ ባነሱት ሃሳብ የሚከተለውን ብለዋል፤ “የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት (River Side Project) ያለምንም ጥርጥር ለብዙ ሀገራት ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ እጅግ አኩሪ ጅማሮ ነው ያለው፡፡ ይህንን አኩሪ ጅማሮ በማስፋት ለመላው ጥቁር ሕዝብ ‘ለካ ይቻላል’ የሚለውን እሳቤ ማስተጋባት ለአዲስ አበባ ይቻላል፡፡”
የመዲናዋ ልማት እና አደባባይ በዓላት
ለጥቁር ሕዝቦች የልማት ተምሳሌት ሆና እየፈካች ያለችው አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያዊያን የጋራ መዲናነቷን የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው፣ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ጥናት ተቋም ትምህርት ክፍል የተግባራዊ ሥነ ልሳን (የፎክሎር) መምህርና ተመራማሪ ግርማ በቀለ (ዶ/ር) መስክረዋል፡፡ በተለይ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች በመዲናዋ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት የበለጠ እንዲደምቁ፣ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም ዘላቂ ትሩፋት እንዲያስገኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ሃሳባቸውን ለማስረዳትም በወርሃ መስከረም በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት የሚከበሩትን የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓላትን በማሳያነት ተጠቅመዋል፡፡

“ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሀገር ናት። እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸው ባህል፣ ዕምነት፣ ቋንቋ፣ እሴት፣ ወግ፣ ሥርዓት… አላቸው። ባህል፣ ዕምነት፣ ቋንቋ፣ እሴት፣ ወግ፣ ሥርዓታቸውን ለማሳየት እና ለሌሎች ለማሳወቅ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ የአደባባይ በዓል ክወና ነው” የሚሉት ግርማ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር በወርሃ መስከረም ላይ በስፋት ከሚከወኑ የአደባባይ (የመስክ) በዓላት መካከል፦ የሽኖዬና ጎቤ፣ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በእነዚህ በዓላት የዕምነቱ ተከታዮች ወይም የአንድ ብሔሩ አባላት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አብረው እንደሚሳተፉ በማንሳት፤ ይህ ደግሞ ለሕዝቦች ትውውቅ፣ አብሮነት፣ አንድነት እና ቅርርብ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ባህል፣ ዕምነት፣ ቋንቋ፣ እሴት፣ ወግ፣ ሥርዓት ለመተዋወቅ እና ለመደናነቅ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር፣ የተደበቀ ባህል የሚታይበት ዕድልን እንደሚያስገኝ ገልፀዋል፡፡ የሕዝቦችን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ አስተሳሰብ፣ አሠራርን እና ስነ ምግባርን ለማሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባን አሁናዊ የልማት እንቅስቃሴ እና ለውጥ፤ በወርሃ መስከረም ከሚታየው ተፈጥሯዊ ገፅታ ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ለአሁኑ የበቃችው ብዙ ችግሮችን አልፋ ነው፡፡ ፅዱ፣ ውብ እና ማራኪ ሆና የተገኘችው የተከማቹ የልማት ጥያቄዎችን ምላሽ ሰጥታ ነው፡፡ ጠባብ ጎዳናዎቿን ያሰፋችው፣ ለሁሉም ማህበረሰብ የምትመች ሆና የተሰኘችው፣ የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ጤናው ተጠብቆ፣ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በስነ ምግባር ታንፆ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረችው፣ የምሽት ጨለማን በዘመናዊ የመብራት ብርሃን የረታችው እልህ አስጨራሽ ተግባራትን በመፈፀሟ ነውም ብለዋል፡፡
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓላት የሚከወኑባቸውን ሥፍራዎች የቀደመ እና አሁናዊ ገፅታ በማነፃፀር ግርማ በቀለ (ዶ/ር) ሃሳባቸውን አብራርተዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ ቀደም ሲል የመስቀል አደባባይን ጨምሮ፤ የአዲስ አበባ መንገዶች እና የጋራ መንቀሳቀሻ (መጠቀሚያ) ሥፍራዎች የተመቹ አልነበሩም። ወንዞቿን መቅረብ ከባድ ነበር። ውሃቸው በጣም የተበከለ፣ ዳርቻቸው ለማረፍ አይደለም ለመንቀሳቀስ የማይመች ነበር። አሁን ግን፤ ነባር አደባባዮች ደረጃቸውን ጠብቀው በዘመናዊ ደረጃ ለምተዋል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተበራክተዋል፡፡ የተለያዩ የአደባባይ (የመስክ) ሁነቶችን በተመቻቸ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችሉ ቦታዎች ተሠርተዋል፡፡ የወንዞች ዳርቻ ልማት አስደናቂ ውጤት እያመጣ ነው። እነዚህ ለውጦች ደግሞ፤ መስቀል ደመራ እና ኢሬቻ የመሳሰሉ የአደባባይ (መስክ) በዓላትን በጥሩ ሁኔታ ለማክበር ያስችላሉ፡፡
እንደመስቀል አደባባይ ሁሉ፤ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ማክበሪያ ቦታ የቀደመ ገፅታ በጣም የማይመች፣ የተበከለ፣ ቆሻሻ የበዛበት እንደነበር ምሁሩ አስታውሰው፤ አሁን ላይ ቦታው በሚገባ ለምቶ እጅግ ውብ፤ ጽዱና ምቹ መሆኑን መስክረዋል። አስተያየታቸውንም በመቀጠል፤ “ኢሬቻ ለኦሮሞ ሕዝብ ባህሉ፣ ዕምነቱ፣ አንድነቱ፣ መሰባሰቢያውና መመካከሪያው ነው። ማንነቱን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ወጉን፣
እሴቱን … ለሌሎች የሚያሳይበት እና የሚያሳውቅበት ነው፡፡ ይህንን አስደናቂ እሴት የተጎናፀፈ እና በጎ ዓላማ ያለውን የአደባባይ በዓል የሚከበርበት ሥፍራ ደግሞ፤ ንፁህ፣ ፅዱ፣ ውብ እና ማራኪ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሠራው ሥራ፤ ለማህበረሰብ ባህል፣ ወግ፣ ማንነት፣ ቋንቋ፣ እሴት እና ሥርዓት የሰጠውን ዋጋ ትልቅ መሆኑን የሚያሳይ እና የሚያስመሰግን ነው” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፤ “አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተካሄደው እና እየተካሄደ ያለው ልማት ለአደባባይ በዓላት ማክበሪያ (መከወኛ) ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ‘መንግስት ለበዓላቱ በአግባቡ መከበር ድጋፍ ማድረግ አለበት’ የሚለውን ሃሳብ በተግባር የመለሰ ሥራ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ መንግስት ይህንን በማድረጉ፤ ራሱም ህብረተሰቡም ይጠቀማል፡፡ ምክንያቱም፤ የአደባባይ በዓላት ለሀገር ዕድገት፣ ለገፅታ ግንባታ፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነት መጎልበት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለሀገር ዘላቂ ልማትና አንድነት ቁልፍ አበርክቶ ያስገኛል፡፡ የቱሪዝም ገቢን ያሳድጋል፡፡” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ