ለህዳሴው ግድብ የተደረገው ህዝባዊ ተሳትፎ ወደፊት በሚካሄዱ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም መደገም እንዳለበት ተመላክቷል
አንዳንዶች ሌላኛው የዐድዋ ድል ነው ሲሉ ይገልፁታል፤ አንዳንዶች ደግሞ የአፍሪካውያን ኩራት ሲሉ ያሞካሹታል፡፡ የሉዓላዊነት ምልክት በማለት የሚገልፁትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተያየት ከሆነ ደግሞ በቅርቡ የተሞሸረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ‘የዘመናት ቀንበር መስበሪያ የታሪክ መታጠፊያ መስመር ነው’።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የኢትዮጵያን ህዝብ ጽናትና ብቃት ሳይ በመሰናሰልና በመደመር ውስጥ ምን አይነት ስራ ሊሰራ እንደሚችል የተማርኩበት ነው” ስላሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲያስረዱም የኢትዮጵያን የዘመናት ፈተና በመተባበር ክንድ እንዴት ማስቀረት እንደተቻለ ትምህርት የሚሰጥ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበት፣ በዲፕሎማሲ ጫና አድራጊነት ተባብረዋል፡፡ ድጋፉ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው የዘለቀ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት የተከበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን የሚያበስረው የሕዝብ ትርዒት በአሁኑ ወቅትም በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች ልዩ የድጋፍ ሰልፎች እየተደረጉ ነው፡፡ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናትም ይቀጥላል፡፡ እስከ አሁን ባለው ጊዜ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የድጋፍ ሰልፉ ተካሂዷል፡፡ በቀጣይ ቀናትም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚካሄድ በመርኃ ግብሩ ተመላክቷል፡፡
“ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን የማንገፋው ተራራ እንደሌለ ማሳያ ነው” ያሉት የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) “ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን የለውጡ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የተደረገው የተቀናጀ ርብርብ የላቀ ድርሻ ተጫውቷል። በዚህም ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በሞራል እና በዲፕሎማሲያዊ ረገድ በአንድነት ቆመዋል” ብለዋል፡፡
ታድያ ይህ የትብብር መንፈስ ኢትዮጵያ ወደፊት ልታከናውናቸው ባሰበቻቸው ሌሎች መሠል ፕሮጀክቶችም ሊደገም የሚገባው እንደሆነ ምሁራን ይመክራሉ። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት ተሳትፎ የነበራቸው እና አሁን በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ዲፕሎማሲ ላይ በአማካሪነት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ እንደሚሉትም የህዳሴ ግድብ ግንባታ የውጭ ድርጅቶችን የገንዘብ ድጋፍ ሳይጠብቅ በራሱ ገንዘብ እንዲገነባ መወሰኑ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር መሠረት ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዲያስፖራዎችን ጨምሮ የገንዘብ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ቦንድ በመግዛት ለግንባታው የሚውል ገንዘብ አሰባስበዋል። ይህ ሂደት ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ገበሬው፣ ተማሪው፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ሀብታሙና ደሃው ሳይባል የፕሮጀክቱ አካል እንዲሆን አስችሏል። ትብብሩ በሌሎች ፕሮጀክቶችም መደገም አለበት።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመረቁበት ዕለት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እውን የሚሆኑ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግባቸውን ፕሮጀክቶች ታከናውናለች፡፡ በተለይ የኒውክሌር ማበልፀጊያ፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጋዝ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና 2ኛው የጋዝ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በልዩ ትኩረት የሚሰራባቸው ፕሮጀክቶች ይሆናሉ። ታድያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የነበረው ትብብር በእነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ መደገም አለበት፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያውያን በትብብርና በአንድነት የመስራት ባህል ከጥንት ጀምሮ የዳበረና በዘመናት ውስጥም የተፈተነ ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረት ያለውና የሃዘንና የደስታ ጊዜን በጋራ መካፈልንም ይጨምራል፡፡ በጋራ አርሶ መዝራት፣ አጭዶ መሰብሰብ፣ ልጆችን መዳር፣ በሃዘን ጊዜ አብሮ ማዘን የአንድ አካባቢ ባህል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤ ነው። ሥነ ልቦናውም መተጋገዝ፣ መተባበር እና በአንድነት የመኖር አስፈላጊነትን መረዳት ላይ የተገነባ ነው፡፡ እንደዚሁም በደቦ ግብርናውን እና ጎጆውን ሲያቀና የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በጋራ ደማቅ ታሪክ ጽፏል፡፡ ይህ በጎ ባህል ወደፊትም መቀጠል እንዲችል መስራት ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የትብብር ቁልፍ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሀገር ስትጠራው ቀድሞ መገኘትን ባህሉ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በኃይማኖት፣ በኑሮ እና በእውቀት ደረጃ ሳይከፋፈል በአንድነት ለልማቱ የተመመበት ነው።
እዚህ ጋር ከዚህ ቀደም የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪ የነበሩት አምባሳደር ስለሺ በቀለ በኢቢሲ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነገን ዛሬ በተሰኘ መሰናዶ ላይ ስለ ግድቡ የተናገሩትን ብንወስድ ግድቡ በኢትዮጵያውያን ላብ እና ደም የተገነባ የወል ታሪካችን፣ የጋራ ምልክታችንም ነው ያሉትን እናገኛለን።
ሰራተኞች ከደመወዛቸው ላይ የተወሰነውን በመቀነስ ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ይህም ህዝቡ ለግንባታው ያለውን ቁርጠኝነትና የባለቤትነት ስሜት አሳይቷል። እንደዚሁም የተለያዩ ዝግጅቶች፣ የኪነ ጥበብ እና የስፖርት ውድድሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ተከናውነው ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ተሰብስቧል። ከገንዘብ አስተዋጽኦ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሞራል እና የሀሳብ አንድነት አሳይተዋል።
የሉዓላዊነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዚህ ስኬት ሲደርስ እልፍ አዕላፍ ችግሮችንና የሴራ ወጥመዶችን አልፏል የሚሉት አቶ ፈቅአህመድ ወጥመዶቹ ሲታለፉም ኢትዮጵያውያን የነበራቸው ድርሻ ቀላል አልነበረም፡፡ ግድቡን በጋራ ከገነቡ በኋላ ‘የእኛ ግድብ ’በማለት የባለቤትነት ስሜት አዳብረዋል። ይህ ደግሞ በፕሮጀክቱ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ትልቅ የሞራል ጥንካሬ ፈጥሯል። ፕሮጀክቱ በሀገር ላይ ሊደረግ የሚችለውን ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በመቃወም ለብሔራዊ ኩራትና ሉዓላዊነት ምልክት ሆኗል። አሁን ላይ በሀሳብ ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶችም የሀገርን ክብርና ኩራት የበለጠ የሚያሳድጉ እንደመሆኑ እውን እንዲሆኑ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ክንድ ይሻሉ ብለዋል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመንግስት ሰራተኛው፣ አርሶ አደሩ፣ ፖሊስ እና መከላከያ እንዲሁም ሌላው የማህበረሰብ ክፍል በ8100 የሞባይል አጭር የጽሑፍ መልዕክት ብር በመላክ፤ እናቶች ካላቸው ጥቂት ገንዘብ በተደጋጋሚ ድጋፍ በማድረግ ተሳትፏቸውን አሳይተዋል። ህይወታቸው ካለፈ በኋላም ለህዳሴ ግድብ ሀብት ንብረታቸውን የተናዘዙ እንደነበሩም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በግል ስራ የተሰማራው ወጣት ሰረበ የሺነህ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳቡን ሲገልጽ፣ በተለያየ ወቅት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዢ መፈፀሙን ገልፆ፣ ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ስለመሆኑ ጠንካራ እምነት እንዳለው ያስረዳል፡፡ የትምህርት ወቅት መገባደድን እየጠበቀ ለማበረታቻ ይሆን ዘንድ ለልጆቹ የህዳሴ ግድብን ቦንድ በስማቸው ገዝቶ ይሰጥ የነበረው ለዚሁ እንደሆነ ያብራራል። አያይዞም የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ፣ የአብሮነትና ብሔራዊ ዓርማ የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለማየት በመብቃቱ ደስታውን ገልጿል፡፡ ይህን አስተዋፅኦ ወደ ፊት በሚካሄዱ መሠል ፕሮጀክቶችም ለመድገም ቁርጠኛ እንደሆነ ነግሮናል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የሀገራቸውን አቋም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በማስተጋባት ለግድቡ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሰጥተዋል። በአስር ዓመት የሳኡዲ ቆይታቸው ለግድቡ የነበራቸውን ድጋፍ አቋርጠው የማያውቁት አቶ አህመዲን ሰይድም እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከምድሯ በፈለቀው የዓባይ ወንዝ ሳትጠቀም የበይ ተመልካች ሆና የቆየችባቸው ዘመናት እያስቆጫቸው እንደቆየ ይገልጻሉ፡፡
ባለፉት ዓመታትም የቦንድ ግዢ በመፈጸም ቁጭታቸውን ስለመወጣታቸው ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በመላው ሀገሪቱ ከፍ ብሎም በውጭው ዓለም በጋራ በአንድነት በመቆም ከዘመናት በፊት በሀሳብ ጥንስስ የነበረው ታላቁ ግድብ እውን ሲሆን ድርሻቸውን በመወጣታቸው ልዩ ስሜት ይሰማቸዋል።
ልክ እንደ አቶ አህመዲን ሁሉ በመላው የዓለም ክፍል የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግድቡን ቦንድ በመግዛት፣ በፕሮጀክቱ ላይ ገንዘብ በመለገስ እና በተለያዩ መንገዶች የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።
‘የዓባይ ፖለቲካና የባዕዳን ተልዕኮ’ መጽሐፍ ደራሲ ስላባት ማናየ በማህበራዊ ትስሰር ገፁ ባሰፈረው መልዕክት፣ ግድቡ ኢትዮጵያ ሀገራዊ እቅዶቿን በራሷ አቅም መፈጸም እንደምትችል ማረጋገጫ ነው። በተለይም ህዝብ በአንድነት ሲቆም በቀጣይም ሊኖሩ የሚችሉ ጫናዎችን ተቋቁሞ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው ሲል አስፍሯል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ