“ሀገሬ የላከችኝ ውድድሩን ለመጀመር ብቻ ሳይሆን ውድድሩን ለመጨረስ ነው።” የሚለው የታንዛኒያዊ የማራቶን ሯጩ ጆን እስጢፋኖስ አኽዋሪ ዘመን ተሻጋሪ ንግግር ዛሬም ድረስ በአስተማሪነት ይጠቀሳል፡፡ በማራቶን ሯጩ ጆን እስጢፋኖስ እ.ኤ.አ በ1968 በሜክሲኮ ከተማ በተደረገው ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ተካፍሎ ነበር።
በውድድሩ ወቅት ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር ተጋጭቶ መሬት ላይ በመውደቅ ጉልበቱን እና ትከሻውን በእጅጉ ተጎዳ፤ ብዙዎች ውድድሩን ያቋርጣል ብለው ሲያስቡ፣ ህክምና ከተደረገለት በኋላ በከባድ ህመም ውስጥ ሆኖ ውድድሩን ቀጠለ። በመጨረሻም ውድድሩን ከአሸናፊው ኢትዮጵያዊው አትሌት ማሞ ወልዴ ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይቶ የጨረሰ የመጨረሻው ሯጭ ሆኖ ነበር። ስታዲየም ሲደርስ ሜዳሊያዎች ተበርክተው የነበሩ ሲሆን፣ አብዛኛው ተመልካችም ስፍራውን ለቆ ነበር። ሆኖም የቀሩት ጥቂት ተመልካቾች በታላቅ ጭብጨባ ተቀብለውታል። በኋላ ላይ ጋዜጠኞች ለምን በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ውድድሩን እንዳላቋረጠ ሲጠይቁት ነበር፣ “ሀገሬ የላከችኝ ውድድሩን ለመጀመር ብቻ ሳይሆን ውድድሩን ለመጨረስ ነው።” የሚል ምላሽ የሰጠው፡፡
ብዙዎችን ያስደነገጠው፣ “ሶሰቱም ኢትዮጵያውያን የማራቶን ሯጭ አትሌቶች ውድድሩን አቋረጡ” የሚለው ዜና የተሰማው ደግሞ ኢትዮጵያ ለዓመታት አንፀባራቂ ጀብዱ ስትፈፅም በኖረችበትና ሰሞኑን ሲካሄድ በቆየው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ነበር፡፡ ከጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ እስከ ቀነኒሳ በቀለ ከመሠረት ደፋር እስከ ጥሩነሽ ዲባባ ሀገሪቱ በሩጫ ብዙ ሜዳሊያዎችን በመሠብሰብ ታዋቂና ተጠባቂ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡ በተለይ የአረንጓዴ ጎርፍ ዘመን ኢትዮጵያ የብዙ ሜዳሊያዎች ባለቤት እንደነበረች የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የአትሌቶች ምድር እየተባለች ትሞካሽ የነበረችው ኢትዮጵያ የ2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ብዙዎችን አንገት ያስደፋ ውጤት አስመዝግባለች። ውድድሩ በከፍተኛ ተስፋ የተጀመረ ቢሆንም፣ በመጨረሻም ውጤቶቹ የፍላጎቱን ያህል አለመሆኑ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል። የዓለም ሻምፒዮናው ላይ የነበረው ተሳትፎ በእርግጥም የሚጠበቀውን ያህል አልነበረም። በተለይ እንደ ማራቶን እና የትራክ ርቀቶች ባሉ ዋና ዋና ውድድሮች ላይ የነበረው አፈጻጸም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የወደፊት እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በዚህ ታላቅ የአትሌቲክስ መድረክ የመጀመሪያውን ወርቅ ያገኘችው የጀርመኗ ከተማ ስቱትጋርት ባዘጋጀችው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲሆን፣ የዚህ ድንቅ ታሪክ ባለድል ደግሞ በ10 ሺህ ሜትር የተሳተፈው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተከናወኑ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ ወርቅ ብርቅ ሆኖባት አያውቅም፡፡ ነገ በሚገባደደው የቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና ላይ ግን ወርቅ ከኢትዮጵያ ላይ ፊቱን ያዞረ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓመታት የነገሰችበት የማራቶን ውድድር ሳይቀር ከእጇ ወጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች ያስመዘገቡት የሜዳሊያ ብዛት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ (ይህን መረጃ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ ሁለት ብር እና አንድ ነሐስ)፣ በተለይ በሴቶች ማራቶን ውድድር ላይ ትግስት አሰፋ የብር ሜዳሊያ ብታገኝም፣ ከኬንያዋ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ጋር በነበራት የቅርብ ፉክክር ወርቁን ማሸነፍ ሳትችል ቀርታለች። እንዲሁም የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ የነበረው ተሳትፎ የኢትዮጵያን ስም አስጠብቆ ቢገኝም፣ ከወርቅ ይልቅ የነሐስ ሜዳሊያውን እንጂ ሌላ ለማስመዝገብ አልተቻለም።
በርካታ አትሌቶች ምንም እንኳን ጥሩ ፉክክር ቢያደርጉም፣ የመጨረሻው መስመር ላይ የነበራቸው ጥረትና ጥራት በቂ አልነበረም። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው የዝግጅት ክፍተቶች፣ የፉክክር ብቃት ማነስ ወይም ደግሞ የውድድር ስልት ላይ የነበሩ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው የሚለው ደግሞ አትሌቲክስን በመዘገብ ለዓመታት የሰራው የስፖርት ጋዜጠኛው ወርቅነህ ጋሻሁን ነው።
የዓለም ሻምፒዮናውን ሲከታተል የቆየው የስፖርት ጋዜጠኛው ወርቅነህ አንደሚለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይህንን የአትሌቶች ውሎ በጥልቀት መመርመር ይኖርባቸዋል። እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ውጤት ማምጣታችን ግን እንዲሁ ድንገት የተፈጠረ ሳይሆን ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት የሚገልፀው ጋዜጠኛ ወርቅነህ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ያብራራል፡፡
አትሌቶቹን ወደ ቶኪዮ በተስፋና በስጋት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደሸኛቸው የሚገልፀው ጋዜጠኛው ስጋት አሳድረውበት የነበሩ ምክንያቶችን እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡ አትሌቶች ወደ ቶኪዮ ከማቅናታቸው በፊት በአንድ ርቀት የሚሮጡ አትሌቶች ጭምር ለየብቻ ተበታትነው ልምምድ ይሰሩ እንደነበርና ለዚህም የሴቶች ማራቶን አትሌቶችን በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡ ከአትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ በስተቀር የትራክ አትሌቶች አውራ ጎዳናዎች ላይ ስልጠና ይሰሩ እንደነበር መረጃ እንዳለው ጠቅሶ፣ በተጨማሪም የአየር ሁኔታውን ያላገናዘበ ልምምድ መስራትን (ቶኪዮ ሞቃት እንደሆነ እየታወቀ ቅዝቃዜ ያለባቸው ቦታዎች ላይ መሰልጠን) በምክንያትነት ይገልፃል፡፡
የፌዴሬሽኑ የዕድሜ ገደብ አለመኖር፣ ወጣት አትሌቶች ከማሳደግ ይልቅ በዕድሜ የገፉ አትሌቶች ላይ መተማመን አዲስ ተሰጥኦ እንዲመነምንም ያደርጋል። በተለይ እንደ 5 ሺህ ሜትር እና 10 ሺህ ሜትር ያሉ የትራክ ርቀቶች በቂ የውድድር ዕድል አለመኖር አትሌቶች የፉክክር ልምድ እንዳያገኙ ያደርጋል። ነገር ግን ውድድር በመጣ ቁጥር ምክንያት ከመደርደር በተሻገረ መልኩ በትክክል ኃላፊነት የሚወስድ እና ቁርጠኛ አመራር የሚወስድ ግለሰብ ያስፈልጋል የሚለውም የብዙዎች አስተያየት ነው።
የቶኪዮውን ክራሞት ሲከታተል በሰነበተው በአትሌቲክስ ቤተሰቡ አስተያየት መሠረት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአንድ ባንዲራ በጋራ የሚዋደቁ አትሌቶች ያሉ አይመስሉም፡፡ አትሌቶቹ ላሳዩት ጥረት አድናቆት እንዳለው የሚገልፀው ወጣት እንግዳወርቅ መንግስቱ በበኩሉ፣ አትሌቶቻችን ምንም አይነት አንድነት አይታይባቸውም ነበር። “ያስቆጫል፤ እንዴት ወርቅ ሳንይዝ እንመለሳለን?” በማለት ስሜቱን ይገልፃል።
ሜዳሊያዎች ቢገኙም ወርቅ ባለመኖሩ ብዙዎች መከፋታቸውን ታዝቤአለሁ የሚለው ወጣት እንግዳወርቅ አትሌቶች እንደ ጉዳፍ ጸጋዬ (በ10 ሺህ ሜትር ነሐስ) እና ትዕግስት አሰፋ (በማራቶን የብር) ሜዳሊያ ቢያገኙም፣ በተለይ ትዕግስት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሆና ወርቅ አለማግኘቷ ብዙዎችን አሳዝኗል። በውድድሩ ዋዜማ እውቋ አትሌት ድርቤ ወልተጂ በዶፒንግ ምርመራ ምክንያት ከውድድር መታገዷም እንደዚሁ በብዙዎች ዘንድ ቁጣና ጥያቄዎችን አስነስቷል።
በሩጫ ውድድሮች ወቅት አትሌቶቻችን ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር ሲወዳደሩ የሩጫውን ፍጥነት እና እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ችግር ታይቷል። በተለይ የመጨረሻ ዙር ላይ የሚወሰን የፍጥነት ለውጥ እና የቦታ አያያዝ ላይ ድክመቶች ነበሩ። በአንዳንድ ውድድሮች ላይ የቡድን ስራ መጥፋቱ በግልፅ ታይቷል። ይህም እንደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ባሉ ተቀናቃኝ ሀገራት አትሌቶች በቡድን ሆነው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የመከፋፈል እና የማዳከም ስልት ሲጠቀሙ በግልፅ ታይቷል።
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ችግሩን በትክክል ያወቀው አይመስልም፤ ከሁሉም አስቀድሞ ራሱን መመልከት ይገባዋል የሚለው ጋዜጠኛ ወርቅነህ ወደፊት ከዚህ ችግር ለመውጣት ሊሰሩ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች በዝረዝር አስቀምጧል፡፡
አትሌቶቹ ከትልልቅ ውድድሮች በፊት በብዙ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ እድል መስጠት እና ከውድድሩም በኋላ አፈፃፀማቸውን በመተንተን ድክመታቸውን ማረም ወሳኝ ነው። አሰልጣኞች ራሳቸው ከዘመናዊ የስልጠና ዘዴዎች ጋር ለመተዋወቅ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ ኮርሶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህም በአትሌቶቹ ላይ ያለውን ችግር ለመለየት እና ለመፍታት ያግዛል። የአትሌቶቹን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ የሚከታተሉ የሙያ ባለሙያዎችን ቡድን ማቋቋም ያስፈልጋል። ይህም የአትሌቶቹን ዝግጁነት ደረጃ ለመገምገም እና የሥልጠና መርኃ ግብሮችን ለማሻሻል ይረዳል በማለት ያብራራል።
ጋዜጠኛው በማጠቃለያ ሀሳቡ እንዳሰፈረው ባረጀው ስርዓት እየሄድን አዲስ ነገር ሊመጣ አይችልም፡፡ እኛ አሁንም ጫካ ነው እየሰለጠንን ያለነው። ዓለም ተቀይሯል፡፡ የላብራቶሪ ምርምር እስከማድረግ ተደርሷል፡፡ የዕድሜ ገደቦችን በማስተካከልና በየክልሉ የትምህርት ቤት አትሌቲክስ ውድድሮችን በማበረታታት አዳዲስ ተሰጥኦዎችን ማፍለቅ። አትሌቶች በግልጽነትና በእኩል ተወዳድረው ወደ ብሔራዊ ቡድን እንዲገቡ ማድረግ ይገባል ይላል።
በአጠቃላይ በቶኪዮው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር የተስተዋለውን አጋጣሚ እንደ ትልቅ ትምህርት መወሰድ አለበት። ወደፊት ትልልቅ ውጤቶችን ለማምጣት ከተፈለገ ከዚህ ቀደም የነበሩት ድክመቶች በዘመናዊና ሳይንሳዊ ዘዴዎች ላይ ተመስርቶ መፈታት አለባቸው።
በሳህሉ ብርሃኑ