በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ5ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል የመርሲሳይድ ደርቢ ይጠቀሳል፡፡ የአንድ ከተማ ክለቦቹ ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ጨዋታቸውን ቀን 8፡30 ይጀምራሉ፡፡
ደርቢው የፉክክር ሚዛኑ ወደ ሊቨርፑል ያጋደለ ቢሆንም በጋለ ስሜት የሚከናወን ጨዋታ ነው፡፡ ሊቨርፑል የውድድር ዓመቱን እንከን አልባ በሆነ ውጤት ጀምሯል፡፡
በሊጉ እና በቻምፒየንስ ሊጉ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በድል አጠናቋል፡፡ የአርነ ስሎት ቡድን በብቃት ደረጃ ግን ጥያቄ አለበት፡፡ በተለይ በመከላከሉ ረገድ መሻሻሎችን ካላሳየ ስጋቶች አንዣበዋል፡፡ ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ተቆጥረውባቸዋል፡፡
ቀዮቹ ምንም እንኳን በመከላከሉ ድክመት ቢያሳዩም የማጥቃት ሃይላቸው ግን ለየትኛውም ክለብ የሚያስፈራ ነው፡፡ 12 ግቦችን ተጋጣሚዎቹ ላይ ያሳረፈው ክለቡ በተለይ አዳዲስ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር በደንብ ሲግባቡ ከዚህም በበለጠ የመሻሻል አቅም አለው፡፡
ኤቨርተን በተለየ ስሜት ቢጫወትም ከሊቨርፑል ጥላ ስር አልወጣም፡፡ ቶፊዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ ሊቨርፑልን በአንፊልድ ያሸነፉት ተመልካች ባልታደመበት በ2021 ነበር፡፡ በመጨረሻ 29 የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት ኤቨርተን ማሸነፍ የቻለው ሁለት ጨዋታ ብቻ ነው፡፡
ለክ እንደቡድኑ የአሰልጣኙ ዴቪድ ሞይስ የአንፊልድ ክብረወሰን ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ኤቨርተን ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ ሰንደርላንድ እና ዌስትሃምን እየመሩ 20 ጨዋታ አከናውነው አንፊልድን በአሸናፊነት የለቀቁበት አንድም አጋጣሚ የለም፡፡
ሀይል የተቀላቀለ ፍልሚያ የሚበዛበት ጨዋታው ቀይ ካርድ አያጣውም፡፡ ሁለቱ ክለቦች በግንኙነታቸው ያስመዘገቡት 25 ቀይ ካርድ በሊጉ ከፍተኛው ነው፡፡ ከተመዘዙት ቀይ ካርዶች ውስጥ ሊቨርፑል 14ቱን ኤቨርተን 11ዱን ይጋራሉ፡፡
በጨዋታው በሊቨርፑል በኩል ኤቨርተን ላይ ስምንት ግቦችን ያስመዘገበው ሞሐምድ ሳላህ ፤ በኤቨርተን በኩል የነሃሴ ወር የሊጉ ኮከብ የተባለው ጃክ ግሪሊሽ ይጠበቃሉ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ