በኢትዮጵያ እግርኳስ በእጅጉ የሚወደደውን ያህል ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት አልተቻለም። ለችግሩ በርካታ ምክንያቶች ይቀመጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በሀገሪቱ ትልቅ የመወሰን ስልጣን ያላቸው መሪዎች ትኩረት መንፈጋቸው እንደሆነ ይጠቀሳል።
አሁን ላይ ይህ እነደችግር አይነሳም። መንግስት የማዘወተሪያ ስፍራ በስፋት ከመገንባት ባለፈ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል መቻል ለዓመታት ሲለፉ ለነበሩ ባለሞያዎች ትልቅ የምስራች ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደር ብሔራዊ ቡድን ይኖረናል ማለታቸው ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ገልፀዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ” እንደዚህ ዓይነት ንግግር ከሀገሪቱ መሪ መስማት ያስደስታል። ለእኛ ለባለሞያዎች የሞራል ስንቅ ይሆናል።” በማለት ተናግረዋል።
ኢንስትራክተር አብርሃም በረጅም ጊዜ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በመንግስት ደረጃ መረዳት መኖሩ አበረታች ነው ብለዋል።
አስፈላጊ ግብዓት ከተሟላ እና በእቅድ ከተመራን በ10 ዓመት ውስጥ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደሚቻልም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአህጉራዊ መድረክ የራቀው ብሔራዊ ቡድን የአሰራር ችግሮች ከተፈቱለት እና ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ በቂ ባለሞያዎች ማፍራት ከተቻለ ተፎካካሪ መሆን እንደሚቻል አንስተዋል።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት እየተገነቡ ያሉት ሜዳዎች ለውጥ ለማምጣት አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
መንግስት ከዚህ ቀደም ትኩረት ተነፍጓቸው ብቻ ሳይሆን የነበሩትም ለሌላ አላማ እየዋሉ የነበሩ ሜዳዎች መመለሳቸው ትልቅ እርምጃ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት አንዱ ግብዓት ታዳጊዎች የሚጫወቱበትን ሜዳ ማዘጋጀት ነው። እዚህ ላይ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ ሁሉም ሊያግዘው እንደሚገባ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጠቁመዋል።
በሸዋንግዛው ግርማ