ኪን-ኢትዮጵያ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የጥበብና ባህል ጉዞ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ባህላዊ የሙዚቃ ምሽት አዘጋጅቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኪን-ኢትዮጵያ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የጥበብና ባህል ጉዞ በቻይናና ሩሲያ የጥበብ ዝግጅቱን በስኬት አቅርቦ ተመልሷል፡፡

መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የጥበብና የባህል ጣዕም፣ ጥልቀትና ውበት ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ ስኬታማ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
የብዙ ሀገሮችን ባህል፣ ቋንቋና እሴት በፊልሞቻቸው፣ በሙዚቃዎችና በሌሎች የጥበብ ሥራዎቻቸው እናውቃለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በጥበብ ለማሳወቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
የባህል ዲፕሎማሲ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የማጠናከር አቅም እንዳለው በማንሳት፤ በባህላችንና በጥበባችን የኢትዮጵያ እምቅ አቅም ለማሳየት መንገድ መጀመሩን ተነግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመስከረም ወር የአዲስ ዓመት መባቻ፣ የአዲስ ተስፋና ብርሃን ማያ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሀገራችን በዓላት በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመዘገቡና በሂደት ላይ እንዳሉም ገልጸዋል።
የመስቀልና ደመራ፣ ኢሬቻ እና ሌሎችም በዓላት የዓለምን ጎብኚዎች የመሳብ አቅም ያላቸው የቱሪስት ሀብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መስከረም የኢትዮጵያውያን የተስፋና ብሩህ ጊዜ የመሻት ወር መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን በዓላት ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል ስራ ጀምረናል ብለዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ነብዩ ተድላ በበኩላቸው፤ የባህል ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት የሚሰራበት አንዱ የዲፕሎማሲ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባህል ዲፕሎማሲ ለህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ በመዲናዋ ለሚኖሩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የቀረበው ዝግጅትም ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው ማለታዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦች፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፤ መርሃ ግብሩ የህዝብ ለህዝብ ትብብር በመፍጠር ለቀጣይ ዲፕሎማሲ ተግባራት መሰረት እንደሚጥል ገልጸዋል፡፡
ኪን ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ጉዞ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት በማቀራረብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲን ያሳድጋል ብለዋል፡፡