ባለፉት የለውጥ አመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንና በሁሉም ኮሌጆች የቅበላ አቅም ማደጉን አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ

You are currently viewing ባለፉት የለውጥ አመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንና በሁሉም ኮሌጆች የቅበላ አቅም ማደጉን አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ

AMN – መስከረም 10/2018 ዓ.ም

ባለፉት የለውጥ አመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንና በሁሉም ኮሌጆች የቅበላ አቅም ማደጉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ስልጠና ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን 7 ሺህ 149 ተማሪዎችን አስመርቀዋል፡፡ የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፤ የዘንድሮ ተመራቂዎችን ልዩ የሚያደርጋችሁ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት መመረቃችሁ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት የተመረቁ ሰልጣኞች ከ 6 ፖሊ ኮሌጆች እና ከ 8 ኮሌጆች፤ በ46 የሙያ አይነቶች፣ ከደረጃ ከሁለት እስከ ደረጃ 5 ከአንድ አመት እስከ 3 አመታት ስልጠናቸውን በብቃት ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በቆይታቸው 30 በመቶውን በማሰልጠኛ ኮሌጆች ውስጥ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ 70 በመቶውን ደግሞ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተመድበው በትብብር የተግባር ስልጠና ልምምድ ያጠናቀቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ጥራቱ አክለውም፤ በከተማችን በሚገኙ 14ቱም ኮሌጆች የሚሰጡ የሙያ ስልጠናዎች የነበሩባቸውን ችግሮችን በመቅረፍ፣ ጥራታቸውን ለማስጠበቅ ሀብት መመደብን እና የሰው ሀይል ማሟላትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት የለውጥ አመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንና በሁሉም ኮሌጆች የቅበላ አቅም ማደጉን አቶ ጥራቱ ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው አመት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 7 ሺህ 149 ሰልጣኞች መመረቃቸውን ያመላከቱት የቢሮ ሀላፊው፤ ይህን ማድረግ እንድንችል ድጋፍ ላደረጉልን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ለሌሎች አካላትም ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡

ተመራቂዎችም በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪና ቀጣሪ በመሆን ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ አቶ ጥራቱ አሳስበዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review