የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ፣ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን የቁጥጥር መምሪያ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን በጥምር ባካሄዱት ኦፕሬሽን ከ303 ሚሊዮን 443ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን ሙሉ ወረዳና ሱመዳዮ ቀበሌ ውስጥ መያዛቸዉን ፖሊስ አስታዉቋል፡፡
ሲጋራና ሺሻዎች፣ ጊዜ ያለፋባቸው መድሀኒቶች ፣ የውበት መጠበቂያ ኮስሞቲክሶች፣ ቦንዳና አዳዲስ አልባሳቶች፣ የተሽከርካሪ ስፔርፓርቶችና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል ናቸዉ፡፡

የፀጥታ አካላቱ በ18 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተጫነውን የኮንትሮባንድ ዕቃ ለአዋሽ ሰባት ጉሙሩክ ቅርንጫፍ መጋዘን ገቢ ማድረጋቸዉና ተጠርጣሪ ኮንትሮባንድስቶችም ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮንትሮባንዱ ሊያዝ የቻለው የፀጥታ አካላቱ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በጋራ በመሆን ባካሄዱት ጠንካራና የተጠና ኦፕሬሽን መሆኑን ገልፀጾ ህብረተሰቡ ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ጫና በመገንዘብ በቀጣይም የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።