በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ እና የቻይናን ኢኮኖሚያዊ ትብብር በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ጉብኝት በቤጂንግ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና በሚኖረው ቆይታም፤ ከሀገሪቱ ዋና ዋና የመንግሥት እና የንግድ አጋሮች ጋር ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚሁ መሠረትም ልዑኩ ከቻይና ፋይናንስ ሚኒስቴር፣ ከቻይና ሕዝብ ባንክ፣ የቻይና ወጪ እና ገቢ ንግድ (ኤግዚም) ባንክ እንዲሁም ከፋይናንስና የንግድ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሚመክር ይሆናል።
በውይይቱ ላይም፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማነት ብሎም እያስመዘገበ ያለውን ስኬት እንዲሁም በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ልዑኩ ገለጻ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ከቻይና እና አጋሮቿ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ተጠቁሟል።
ጉብኝቱ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት የሚያጎላ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ወደ ማሳደግ እና ለቀጣይ ትብብር ጠንካራ መሰረት ለመገንባት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።