የአደባባይ በዓላት እሴታቸውንና ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ሴቶች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አሳስቧል፡፡
ቢሮው የ2018 ዓ.ም የመስከረም ወር የአደባባይ በዓላትን አስመልክቶ ከሴቶች ማህበር ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመስከረም ወር የሚከበሩት የመስቀል ደመራ እና የሆረ-ፊንፊኔ ኢሬቻ የአደባባይ በዓላት እሴታቸውን እና ትውፊታቸውን በጠበቀ መልኩ ተከብረው እንዲጠናቀቁ ሴቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የቢሮ ሀላፊዋ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አሳስበዋል።
በዓሉ በርካታ እንግዶች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሴቶች ማህበር በሰላም አደረጃጀት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ሴት ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ እናታለም እንዳለ ናቸው።
የማህበሩ ሴት አባላት ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ከበዓሉ ቀደም ባሉት ቀናት ጀምሮ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው ”በእምርታና ማንሰራራት የታጀበ ህዝባዊ በዓላትን በጋራ እናክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ከሴቶች ማህበር አመራሮች እና አባላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በአይናለም አባይነህ