እየጨመረ የመጣው የፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ጠቀሜታ እና አንድምታ

You are currently viewing እየጨመረ የመጣው የፍልስጤም የሀገርነት እውቅና ጠቀሜታ እና አንድምታ

AMN – መስከረም 12/2018 ዓ.ም

ለበርካታ አመታት ግጭት የሰነበተባት ፍልስጤም ከእስራኤል ጋር ሰላማዊ የጉርብትና ኑሮን ትመራ ዘንድ ራሷ የምታስተዳድረው የተከለለ ድንበር እንዲሰጣት ከተጠየቀ ሰነባብቷል።

“ቱ ስቴት ሶሉሽን” (የሁለት ሀገርነት መፍትሄ) በመባል የሚታወቀው ሀሳብ የጸደቀው በ1993 በኦስሎ ዲክላሬሽን ሲሆን ነገር ግን በወቅቱ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

“ፍልስጤም የሚባል ሀገር የለም” በሚል አቋሟ የጸናችው እስራኤል በዌስት ባንክ የምታደርገውን መስፋፋት ቀጥላለች።

በፍልስጤም ሀገር ሆኖ መመስረት ጉዳይ ሁለቱን አካላት የማያስሟሟቸው ነጥቦች የድንበር ጉዳይ ፣ የወደፊት የአገረ-ፍልስጤም ዕጣ ፈንታ እና አስተዳደር ጉዳይ ናቸው።

በተጨማሪም የእየሩሳሌም ጉዳይ እንዲሁም በእስራኤል ምስረታ ጊዜ የተሰደዱ የፍልስጤም ስደተኞች ነገርም አከራካሪ ነጥቦች ሆነው ቀጥለዋል።

ምንም እንኳን ከ193 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ከ150 በላይ ሀገራት ለፍልስጤም እውቅና ቢሰጡም ድርጅቱ እስካሁን ነጻ ሀገር መሆኗን አላወጀም።

ከሰሞኑ የቡድን 7 አባል ሀገራት ጭምር ባልተጠበቀ ሁኔታ ለፍልስጤም እውቅናን እየሰጡ ይገኛሉ። በትላንትናው ዕለት ካናዳ ፣ አውስትራሊያ እና ብሪታንያ እውቅና መስጠታቸው ይታወቃል።

በፈረንሳይ እና ሳኡዲ አረቢያ አማካኝነት እየተመራ በሚገኘው ዘመቻ ማክሰኞ በሚጀመረው 80ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ፈረንሳይን ጨምሮ 5 ሀገራት እውቅናቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

👉ለፍልስጤም እየተሰጠ የሚገኘው እውቅና መሬት ላይ ያለው ተጽዕኖ እና ጠቀሜታ

እውቅና የሚሰጡ ሀገራት በቆንጽላ ደረጃ ያላቸውን ውክልና ወደ ኤምባሲ ሊያሳድጉ እንደሚችሉ፣ የሌላቸውም በፍልስጤም ግዛት ውስጥ አዲስ ኤምባሲ ሊከፍቱ ይችላሉ።

ይህም አሁን ያለው የፍልስጤም መንግስት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ሀገር ለመምራት ያለውን ታአማኒነት የሚያሳድግለት ነው።

በአሁኑ ወቅት 40 የሚደርሱ ሃገራት በራማላህ እና ዌስት ባንክ በተወካይ ደረጃ የሚመራ ቆንጽላ አላቸው።

ሆኖም ፍልስጤም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙሉ አባል እስካልሆነች እና ራሷ የምታስተዳድረው የተከለለ ድንበር እስከሌላት ድረስ የተሟላ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማድረግ ትቸገራለች።

እስራኤል እውቅናውን ተከትሎ ኢንቨስትመንት ፣ ትምህርት እና የሸቀጦች ግብይትን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎትን ብታግድ ፍልስጤም ሀገር ሆና ለመዝለቅ ትቸገራለች ሲል ሮይተርስ አስነብቧል።

ዘገባው ሲቀጥል ፍልስጤም የሁሉንም የተመድ አባል ሀገራት እውቅናን ብታገኝም በጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ወደ ሙሉ አባልነት እስካልተቀየረች ድረስ እውቅናው በእስራኤል ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ከመፍጠር ባለፈ እምብዛም ጠቀሜታ አይኖረውም ሲል አክሏል።

ውሳኔው ለምክር ቤቱ በሚቀርብበት ጊዜ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት አሜሪካ፣ የሀገርነት ምስረታው በእስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር ላይ ካልተመሰረተ ከፍልስጤም ሀገር ሆኖ መመስረት ሀሳብ ተቃራኒ ሆና መቆሟ አይቀሬ ነው ተብሏል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review