ከልምምድ አርፋጅነት ወደ ባሎን ድ ኦር አሸናፊነት

You are currently viewing ከልምምድ አርፋጅነት ወደ ባሎን ድ ኦር አሸናፊነት

AMN-መስከረም 13/2018 ዓ.ም

“በትክክል ከተጠቀምንበት የዓለም ምርጡ ተጫዋች ይሆናል።” ዣቪ ኸርናንዴዝ የባርሰሎና አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ስለ ኡስማን ዴምቤሌ የተናገረው ነው።

ዣቪ በተጫዋቹ ላይ የተመለከተው ተሰጥኦ ትልቅ ደረጃ እንደሚያደርሰው እምነት ነበረው። ብዙዎችን ያስገረመው ግን በወቅቱ ዴምቤሌ ከመሻሻል ይልቅ ለመጥፋት የተቃረበ በመሰለበት ወቅት ዣቪ እንዲህ መናገሩ ነው። ዴምቤሌ በእግርኳስ ሕይወቱ ከፍታ እና ዝቅታው ተመልክቷል። በስታደ ሬኔ ያሳየው ብቃት ቦሩሲያ ዶርትመንድ ከበርካታ ክለቦች ጋር ተፎካክሮ እንዲያስፈርመው ያስገደደ ነበር።

ባርሰሎናም በ2017 ኔይማርን ሲያጣ በወቅቱ የዓለም ሁለተኛ ውዱ ተጫዋች አድርጎ በ135 ሚሊየን ፓውንድ ያስፈረመው በተሰጥኦ ጥርጣሬ ስላለነበረው ነው። ለዴምቤሌ ግን ነገሮች ቀላል አልሆኑለትም። በተወራለት ልክ ተሰጥኦን ማሳደግ አልቻለም። ጉዳት ፣ ለስራው ያለው ትጋት ደካማ መሆን ፣ በልምምድ ቦታ አርፍዶ መገኘት የእግርኳስ ሕይወቱን አቀጭጨው እርሱን ለማስረሳት ተቃርበው ነበር።

ዴምቤሌይ በተለይ በባርሰሎና እያለ በተደጋጋሚ ይገጥመው የነበረው ጉዳት 784 ቀናትን ከሜዳ ውጪ እንዲሆን አድርጎታል። የቪዲዮ ጌም የሚያዝወትረው ተጫዋቹ ምሽት ላይ ተገቢውን እንቅልፍ ስለማይተኛ ሁሌም ልምምድ ላይ እንዳረፈደ ነው። በካታሎኑ ክለብ ውስጥ እንደርሱ በማርፈድ ብዙ ገንዘብ የተቀጣ ተጫዋች የለም።

የኡስማን ዴምቤሌ ሊጠፋ የነበረውን የእግርኳስ ሕይወት የቀየረችው የአሁኑ ባለቤቱ ሪማ ናት። በ2021 በሞሮኮ ያገባት ይህቺ እንስት የሕይወቱ ብርሃን እንደሆነችለት ጉሊዬም ባላጌ ቢቢሲ ስፖርት ላይ ያሰፈረው ፅሁፍ ያመለክታል።

ባርሰሎናን ከመልቀቁም በፊት የጠንካራ ሰራተኝነቱን መንገድ የያዘው ዴምቤሌ የልጅ አባት ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ሃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆነ ይነገርለታል። ኡስማን ዴምቤሌ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ለፍቷል። አመጋገቡ እንዲስተካከል የአካል ብቃቱም እንዲጎለብት በግሉ ባለሞያዎችን ቀጥሮ እየሰራ ይገኛል።

በ2023 በ43.5 ሚሊየን ፓውንድ የተቀላቀለው ፓሪሰን ዠርማ ዓለም የእርሱን ብቃት እንዲገነዘብ መድረኩን አመቻችቶለታል። እርሱም ጠንክሮ ሰርቶ ትናንት ምሽት የተካሄደውን 69ኛውን የባሎን ድ ኦር ሽልማት በማሸነፍ የከፍታውን ጫፍ መንካት ችሏል።

ዴምቤሌ ሽልማቱ ከተበረከተለት በኋላ ሲያነባ ታይቷል። በተለይ የእናቱን ስም ሲያነሳ እምባውን መቆጣጠር አልቻለም። የ28 ዓመቱ ተጫዋች በተለይ ጉዳት ሲያሰቃየው ቀድማ ትገኝ የነበረችው እናቱ ናት። ከፍታውንም ዝቅታውንም ያየው ዴምቤሌ በመጨረሻ ዣቪ ኸርናንዴዝ እና ሌሎች በእርሱ ላይ እምነት የነበራቸው ሰዎች የጠበቁት ከፍታ ላይ ተገኝቷል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review