በውሃ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የደህንነት ስጋቶችን በብቃት ለመጠበቅ የተቋቋመው የባሕር ላይና ዳርቻዎች ጥበቃ ፖሊስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እና ሲፈጸም በብቃት መመርመር የሚያስችል ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደሕንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የውሃ አካላትን ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የባሕር ላይና ዳርቻዎች ጥበቃ (ኮስታል ጋርድ) የተሰኘ የፖሊስ ክፍል መደራጀቱን ጠቅሰዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ሥራ መጀመሩንም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኮስታል ጋርድ ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎችን የታጠቀ መሆኑን በማንሳት፤ ጀልባዎቹ በሐይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደሕንነት ሥጋቶችን መከላከልና በብቃት ምላሽ መስጠት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮስታል ጋርድ አባላት በዘርፉ በቂ ስልጠና ያገኙና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎቹ የክትትል ካሜራዎች፣ የላቀ የመገናኛ ዘዴዎች እና የራዳር ሲስተም የተገጠመላቸው መሆናቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡
ጀልባዎቹ በውሃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችና የደሕንነት ስጋቶችን በብቃት መቆጣጠር እንደሚያስችሉም ነው የተናገሩት፡፡